
ሁመራ: ጥር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እያሳየው ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መኾኑን በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር ገልጿል።
የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ባለፈው 2017 በጀት ዓመት የሕዝቡን መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በመንግሥት እና በሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን አከናውኗል።
በዚህም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው 1 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ 2 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ፣ 8 የመማሪያ ክፍሎች ያሏቸው ሁለት ብሎኮች እና የኮሪደር ልማት አካል የኾነ የከተማ አደባባይ ግንባታዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረእግዚአብሔር ደሴ የዳንሻ ከተማ አሥተዳር የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እያሳየው ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መኾኑን በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል።
በዚህም የከተማዋን የመንገድ መሠረተ ልማቶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በማዘመን እና በሌሎች ግንባታዎች ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ባለፉት አምስት የነጻነት ዓመታት ከሰላም እና ጸጥታ ተግባራት ጎን ለጎን የተከናዎኑ የልማት ሥራዎች አበረታች መኾናቸውንም አቶ ገብረእግዚአብሔር አመላክተዋል።
ከነጻነት በኋላ ራስን በራስ የማሥተዳደርን ዕድል በመጠቀም ከተማዋን እያለሙ መኾናቸውን የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አብዱልዋሃብ ማሙ ተናግረዋል።
ከተማዋን የኢንቨስትመንት ከተማ ለማድረግም እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።
ዳንሻን የኢነቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ለ30 አልሚ ባለሃብቶች ከ55 ሺህ 800 ካሬ ሜትር በላይ ቦታዎችን በማዘጋጀት ምቹ ኹኔታዎችን መፍጠራቸውን አስረድተዋል።
በዚህም አብዛኛዎቹ ባለሃብቶች በተሰጣቸው ቦታ ላይ ወደ ሥራ መግባታቸውንም አቶ አብዱልዋሃብ ጠቁመዋል።
በተከማዋ በተከናዎኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች መሳተፋቸውን እና አካባቢን ማልማት ሁሉንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የከተማዋ ነዋሪዎች አንስተዋል።
የከተማዋን ልማት ለማስቀጠል ቁርጠኛ ማኅበረሰብ መኖሩንም ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።
ዘጋቢ፦አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
