ለ40 ሺህ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የግብርና ብድር ሊቀርብ ነው።

3

 

ደብረብርሃን: ጥር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብረ ብርሃን ዲስትሪክት በቀጣዮቹ ሦሥት ወራት ለ40 ሺህ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የግብርና ብድር አቅርቦትን ለማቅረብ መዘጋጀቱን ገልጿል።

ዲስትሪክቱ ከደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ እና እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት መምሪያ ጋር የግብርና ብድር አቅርቦት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱ በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ አርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን በግብርና ብድር ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ምርታማነትን ብሎም ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መኾኑ ተብራርቷል።

በስምምነቱ ላይ የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የግብርና ታሪክ አላት ብለዋል።

ይሁን እንጅ አሁንም ግብርናው ከኋላቀር አሠራር አልተላቀቀም፤ ለዚህ ደግሞ ዘርፉ በሚፈልገው ልክ በፋይናንስ አለመደገፋ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል ነው ያሉት አቶ ወርቃለማሁ።

በመኾኑም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለግብርናው ዘርፍ ይዞት የቀረበው የብድር አቅርቦት ዘርፉን ለማዘመን እና የአርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ በግብርናው ዘርፍ የሜካናይዜሽን ፍላጎቶች ስላሉ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ዕድሉን በተገቢው እንዲጠቀሙ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብረ ብርሃን ዲስትሪክት ዳይሬክተር ሮቤል ጨበር ባንኩ ያስጀመረው የግብርና ብድር አቅርቦት በዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ የቀረበ መኾኑን ተናግረዋል።

የብድር አቅርቦቱ በግል እና በቡድን የተመቻቸ መኾኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የዕድሉ ተጠቃሚ ለመኾን በማስያዣነት የሚጠየቁት መሬታቸውን መኾኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለግብርናው ዘርፍ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን በላይ ብር በብድር ለማሠራጨት መመደቡም ተመላክቷል::

የባንኩ የዲስትሪክት የሥራ ክፍል ኀላፊዎች፣ የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ እና የመምሪያ ኀላፊዎች በተገኙበት የግብርና ብድር አቅርቦቱ የመግባቢያ ስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓትም ተከናውኗል።

ዘጋቢ፦ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክልሉን ነዋሪዎች የቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታት እየተሠራ ነው።
Next articleየግዥ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ለማቀላጠፍ የወጣው አዋጅ አንደምታ፦