
ባሕር ዳር: ጥር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ከአማራ ክልል መሬት ቢሮ ጋር በመተባበር በቤት ልማት ፓሊሲ ዙሪያ ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር እየመከሩ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ከተሜነት እየተስፋፋ በመምጣቱ ከፍተኛ የቤት ፍላጎት እንዲኖር ምክንያት መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም የቤት ፍላጎት እና አቅርቦቱ እንዳይመጣጠን አድርጓል ነው ያሉት።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን በመጠቀም የዜጎች የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል። በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ጠቁመዋል።
በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የቤት ልማት ፖሊሲ መጽደቁንም አንስተዋል። በክልል ደረጃ የቤት ልማት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በክልሉ የ25 ዓመታት አሻጋሪ የልማት እቅድም በትኩረት ተይዞ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ውጤታማ የቤት ልማትን ለማሳካት ለቤት ልማት አስፈላጊ የኾኑ የመሬት፣ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጅ አቅርቦትን በመለየት መሥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) የቤት ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም በዜጎች ላይ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚዳርግ ተናግረዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የፋይናንስ ውስንነት፣ ሕገ ወጥ የቤት ግንባታ መበራከት እና የመሬት አቅርቦት ችግሮች እንቅፋት መኾናቸውንም ጠቁመዋል።
ያለፉትን አፈጻጸሞች በመገምገም እና የቤት ልማት ፖሊሲውን በሚገባ ተገንዝቦ ተግባራዊ በማድረግ ለዘላቂ መፍትሄ ርብርብ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
