ሥልጡን ሕዝብ እና ሥልጡን ከተማ ለመገንባት ሥልጡን አሥተዳደር ሊኖር ይገባል።

3
ወልድያ: ጥር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውል የከተማ አውቶብስ ሥራ አስጀምሯል።
ሥራ የጀመሩት ሦስት አውቶብሶች በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ በመኾናቸው ኃይልን ለመቆጠብ እና አካባቢን ከብክለት ለመታደግ ሚናቸው የጎላ እንደኾነ ተገልጿል።
የወልድያ ከተማ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ሀጂ ሲራጅ አደም ወልድያ ከተማ ገጽታዋ ተቀይሯል፤ ይህ ዘመናዊ አውቶብስም ከተማዋን ለማዘመን የራሱን መልክ ይዞ የተከሰተ ነው ብለዋል።
የወልድያ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አሥኪያጅ መጋቢ ጥበባት አክሊለብርሃን ተመስገን የሕዝብ አውቶብስ ከከተማ ገጽታ እና ከትራንስፖርት ችግር መቅረፍ ባሻገር ማኅበራዊ ትስስርን ለመፍጠር አጋዥ መኾኑን ገልጸዋል።
በአንድ አውቶብስ የሚጓዙ የአንድ ከተማ ነዋሪዎች በጉዟቸው የተለያዩ ጉዳዮችን እያወሱ ማኅበራዊ ጉዳያቸውን የሚመክሩበትን አጋጣሚ ይፈጥራል ነው ያሉት።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ “ሥልጡን ሕዝብ እና ሥልጡን ከተማ ለመገንባት የሠለጠነ አሥተዳደር ሊኖር ይገባል” ብለዋል።
አሥተዳደር ሢሠለጥን ከጊዜው ጋር የሚራመድ የኅብረተሰብን ኑሮ ለማቅለል የሚያስችሉ አገልግሎትን መዘርጋት አለበት ነው ያሉት። ወልድያ ከተማ አሥተዳደርም የነዋሪዎችን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ከመዘኑ ጋር የዘመኑ አውቶብሶችን ለኅብረተሰቡ አበርክቷል ነው ያሉት።
ከተሞች እርጅና በቃን ሲሉ ነዋሪዎቹ እና መሪዎቹ ከእርጅና በማላቀቅ የማዘመን ኀላፊነታቸውን የመወጣት ግዴታ አለባቸው ብለዋል።
ሦስቱ አውቶብሶች ከባጃጅ አገልግሎት ጎን ለጎን አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡም ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ ሀብቱን በእኔነት ስሜት እንዲጠብቅም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምክክር አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ዋነኛው መፍትሔ ነው።
Next articleየፋይናንስ እምርታ በኢትዮጵያ