ምክክር አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ዋነኛው መፍትሔ ነው።

6
ባሕር ዳር: ጥር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላምን ማፅናት፣ ጸጋን ማልማት” በሚል መሪ መልዕክት
በአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የፓናል ውይይት በባሕርዳር እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ በክልሉ እምቅ ሃብቶች ዙሪያ የተዘጋጁ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ የአማራ ክልል የተለያዩ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤት ቢኾንም ታሪካዊ ጠላቶች ጸጋዎቹን አልምቶ እንዳይጠቀም ሲሠሩ ቆይተዋል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳት አስከትሏል ነው ያሉት። ይሁን እንጅ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተሠራው ሥራ ችግሩን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።
የጠላቶችን ሴራ ከማክሸፍ ባለፈ ሀገር በቀል የፖለቲካ እሳቤ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሪፎርም በመቅረጽ ታላላቅ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል።
ክልሉ ያለውን እምቅ ሃብት በተሟላ መንገድ ለማልማት ደግሞ ሁሉም ኀላፊነት ወስዶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የሕዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ እና የሀገሪቱን ገጽታ የሚቀይሩ ትላልቅ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
ሀገሪቱ ያላትን እምቅ ሃብት በዘላቂነት ለማልማት ደግሞ ሰላምን ማጽናት ተቀዳሚው ተግባር መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኀላፊነት ወስዶ መሥራት እንዳለበት አንስተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ እውነቴ አለነ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት የሕዝቡን መከራ ከማራዘም ያለፈ ለውጥ አለማምጣቱን አንስተዋል።
በሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ምክክር ዋነኛው መፍትሔ መኾኑንም ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ባለፉት ሦሥት ዓመታት በሠራው ሥራ የፖለቲካ ባሕልን መቀየር መቻሉን ነው የገለጹት። ከምክክር ባለፈ መፍትሔ ተኮር ለውጦች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሀገሪቱን የሚመጥን አጀንዳ መሠብሠብ መቻሉንም ጠቁመዋል። አሁን ላይም አጀንዳ ያላቀረበ ማንኛውም አካል እስከ መጨረሻው ማቅረብ እንደሚችልም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ የጎንደር አብያተ መንግሥታትን ጎበኙ።
Next articleሥልጡን ሕዝብ እና ሥልጡን ከተማ ለመገንባት ሥልጡን አሥተዳደር ሊኖር ይገባል።