
አዲስ አበባ: ጥር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን እና አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት በኩል ላበረከተው አስተዋጽኦ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እውቅና ተሰጥቶታል።
እውቅናውን የሰጡት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ሚዲያው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን በልዩ ቀለም በድምቀት እንዲከበር አሚኮ ሰፊ ሽፋን መስጠቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ በማስተሳሰር፣ ኢትዮጵያንም ለዓለም በማስተዋወቅ፣ በሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እና ለማንሰራራት ጉዞ ምቹ መደላድል በመኾን አሚኮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ አስታውቀዋል፡፡
ለበዓሉ በስኬት መከበር አስተዋጽኦ ያደረጉ ተቋማትንም አመስግነዋል።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሥተባባሪነት እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ አስተናጋጅነት “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሆሳዕና ከተማ መከበሩ ይታወሳል፡፡
ዘጋቢ:- ኢብራሒም ሙሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
