
ደብረ ማርቆስ: ጥር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ዞን አቀፍ የባሕል፣ የሙዚቃ እና የቲያትር ፌስቲቫልን በደብረ ማርቆስ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
የመምሪያው ኀላፊ ብርቄ ይዘንጋው ዞኑ ለሀገራችን የኪነ ጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋጾ ያላቸው፤ አይረሴ ሥራዎችን ያበረከቱ፤ በርካታ የኪነ ጥበብ ሰዎችን ያፈራ እና አሁንም በማፍራት ላይ ያለ መኾኑን ተናግረዋል።
ኪነ ጥበብ ለዞኑ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት አስተዋጾኦ እንዲያበረክት ለማስቻል ፌስቲቫሎችን እና የፈጠራ ውድድሮችን ሲያዘጋጅ መቆየቱንም መምሪያ ኀላፊዋ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በዞኑ የተካሄዱ የባሕል ፌስቲቫሎች የዞኑን ሕዝብ ባሕል በማስተዋወቅ እና ገጽታን በመገንባት፣ ባሕላዊ እና ኪነ ጥበባዊ ሃብቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል ብለዋል።
እየተካሄደ ያለው የባሕል እና ኪነ ጥበባት ፌስቲቫል በተለያዩ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ላይ የሚያተኩር ሲኾን ፌስቲቫሉ የሙዚቃ እና የቲያትር ዝግጅቶችን አጣምሮ የያዘ መኾኑም ተገልጿል።
ፌስቲቫሉ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ መቆየቱንም ኀላፊዋ አንስተዋል።
ኪነ ጥበብ ከማዝናናት ባለፈ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ኅብረተሰቡን በማስተማር የተሻለ ግንዛቤ እና አመለካከት እንዲፈጠር በማድረግ ጠንካራ ሀገራዊ መግባባትን ለመገንባት ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ እና ለልማት ሥራዎች አጋዥ መሳሪያ በመኾኑ የፈጠራ ሥራዎችን በማበርታት እና ለባለሙያውች እውቅና በመስጠት ዘርፉን መደገፍ ይገባል ነው ያሉት።
በዕለቱ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋዬ በላይ የባሕል ፌስቲቫሎች ባሕልን ከማስተዋወቅ ባሻገር ሰላምን ለማጽናት፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማሳደግ እና ተተኪ የኪነ ጥበብ ሙያተኞችን ለማፍራት ድርሻው የጎላ መኾኑን ተናግረዋል።
ዞኑ ያለውን እምቅ የኪነ ጥበብ እና የባሕል ሃብት ለማስተዋወቅ ዘርፉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የኪነ ጥበብ ዘርፉን እና የዞኑን እምቅ ባሕል ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው የባሕል፣ የሙዚቃ እና የቲያትር ፌስቲቫል ከዞኑ የተውጣጡ 11 ወረዳዎች እየተሳተፉ ነው።
አሸናፊ የሚኾነው ወረዳ በቅርቡ በክልሉ በሚካሄደው የባሕል እና የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ዞኑን ወክሎ የሚሳተፍ ይኾናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
