የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች እያስተዋወቀ መኾኑን የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።

3
ወልድያ: ጥር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል 108 ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በመስክ እና በቤተ ሙከራ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።
በ2017/18 የምርት ዘመን ሰባት የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች የማስተዋወቅ ሥራ መሠራቱንም አስታውቋል። በተለይም የአርሶ አደሮች ጥያቄ መልስ ያገኘበት አዳዲስ የማሽላ እና የስንዴ ዝርያ ማስተዋወቁ ነው የተገለጸው።
በሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል የማሽላ፣ የጤፍ እና የበቆሎ ተመራማሪ ሙሉጌታ ማሞ ቀደም ብሎ የተዋወቁ ጊራና እና መልካም ማሽላ ዝርያዎች ለእንስሳት ቀለብ የሚኾን የአገዳ እና ጥራት ያለው የእንጀራ ማሽላን ያሟሉ እንዲኾኑ አርሶ አደሮች ይጠይቁ እንደነበር ገልጸዋል።
የአርሶ አደሮችን ችግር የሚፈታ ሲሪንቃ አንድ የተሰኘ አዲስ የማሽላ ዝርያ በምርምር በልፅጎ ለአርሶ አደሮች ማስተዋወቅ ተጀምሯል ነው ያሉት።
ሲሪንቃ አንድ ከ120 ቀን በታች በኾነ ጊዜ ቀድሞ የሚደርስ፣ በሄክታር ከ50 ኩንታል በላይ ምርት የሚሰጥ እና አገዳውም ከሁለት ሜትር በላይ ቁመት እንዳለው ነው ያስረዱት።
ወለዲ እና አምባሰል የተባሉ ሌሎች የማሽላ ዝርያዎች እስከ 130 ቀን የሚደርሱ እና በሄክታር ከ45 ኩንታል በላይ ምርት የሚሰጡ ተጨማሪ ዝርያዎችም ከምርምር ማዕከሉ ወጥተው ለአርሶ አደሮች የማስተዋወቅ ሥራ ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በጤፍ ዝርያ ሙሉጌታ ማማን ከቦሰት እና ቁንጮ ጤፍ ዝርያዎች በማዳቀል የምርት መጠኑ ከአካባቢው ዝርያ 15 እጅ የተሻለ ምርት የሚሰጥ ዛቲ ጤፍ ዝርያ ከማዕከሉ በምርምር ወጥቷል ነው ያሉት።
በምርምር ማዕከሉ የግብርና ምጣኔ ሀብትና ግብርና ኤክስቴንሽን አስተባባሪ እና የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ መኮንን አሰፋ ከነባሩ የዳንፌ ስንዴ ዝርያ በምርታማነቱ እና በምርት ጊዜ ቆይታው የተሻለ የኤልሻሎም ስንዴ በምርምር በልፅጎ ለአርሶ አደሮች ማስተዋወቅ መጀመሩን ለአሚኮ ገልጸዋል።
የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አካሉ ገብሩ በምርምር የወጡት አዳዲስ ዝርያዎች አስፈላጊው ክትትል፣ ሙከራ እና ፍተሻ ተደርጎላቸው ማረጋገጫ የተሰጣቸው መኾናቸውን አስረድተዋል።
ማዕከሉ በምርምር ያገኛቸውን ዝርያዎች ወደ ዘር ብዜት አሳድጎ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት የክልል፣ ዞን እና ወረዳ ግብርና ተቋማት ጋር በጥምረት እየሠራ ነው ብለዋል።
ወደፊት በዘር አምራች አርሶ አደሮች፣ ማኅበራት እና በምርምር ጣቢያዎች የዘር ብዜት እየተሠራ የማሰራጨት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበልማት ሥራዎች ላይ የተቋማት አለመናበብ ለምን?
Next articleየአማራ ክልል የተቀናጀ የገጠር ማዕከላት ቤት ልማት የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።