በልማት ሥራዎች ላይ የተቋማት አለመናበብ ለምን?

3

በልማት ሥራዎች ላይ የተቋማት አለመናበብ ለም

ባሕር ዳር: ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድ ከተማ የመንገድ ልማት ሲለማ የውኃ፣ የማፋሰሻ፣ የመብራት፣ የቴሌ መስመሮች፣ የጽዳት እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች በተቀናጀ ዕቅድ መሠራት እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ። የከተማ መሠረተ ልማቶች ውጤታማ እንዲኾኑም የተቋማት መቀናጀትን፣ መናበብን፣ የጋራ ዕቅድ እና ክትትልን፣ እንዲሁም ለአንድ ዓላማ መቆምን የሚጠይቁ ናቸው።

በባሕር ዳር ከተማ በተለምዶ ገጠር መንገድ ከሚባለው አካባቢ ወደ በላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ የሚወስደው መንገድ በአዲስ መልኩ ተሠርቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾኖ ቆይቷል። ነገር ግን የመንገዱ የመኪና ማቋረጫ ባልተገባ የውኃ ቱቦ ዝርጋታ ምክንያት እንደልብ ለማቋረጥ አስቸጋሪ ከኾነ ወራትን አስቆጥሯል። በአካባቢው ላሉት የተቋማት አሽከርካሪዎችም ፈተና ኾኖባቸዋል።

አቶ ንብረት ካሳሁን አሸከርካሪ ናቸው። መንገዱን ለማቋረጥ ሲሉ ረጅም ርቀት ለመጓዝ እንደሚገደዱ ተናግረዋል። ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው እንደሚያቋርጡም ገልጸዋል። ሥራ ለመሥራት መቸገራቸውንም ገልጸዋል።

በመንገዱ መዘጋት ምክንያትም ለቅጣት መዳረጋቸውን አንስተዋል። ለትራፊክ አደጋ እንደሚያጋልጥም አብራርተዋል። በሚመለከተው አካል በኩል መፍትሄ እንዲፈለግለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

መንገዱን የገነባው የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የባሕር ዳር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ዮሴፍ ወርቁ የውኃ ቱቦው በአስፋልቱ ስር መቀበር የነበረበት መኾኑን አንስተዋል።

ነገር ግን መንገዱ ሲሠራ የውኃ መስመር ዝርጋታው በዲዛይኑ አለመካተቱን አስረድተዋል። ይህም የከተማ አሥተዳደሩ ችግር እንጂ የተቋማቸው ችግር እንዳልኾነ አብራርተዋል። አሁን ላይ ተቋማቸው አስፋልት ቆርጦ የማስተካከል ግዴታ እንደሌለበት አስታውቀዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር አካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጽጌረዳ አበበ የማቋረጫ መንገዱ የተዘጋው ለመንገዱ አካፋይ አትክልቶች በተዘረጋው የውኃ መሥመር ምክንያት መኾኑን ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታት አስፋልቱ ተቆርጦ የውኃው መስመር በስር እንዲዘረጋ እና የተዘጋው ማቋረጫ መንገድ እንዲከፈት በከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ኮሚቴ በኩል አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየላሊበላን የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ለማቃለል እየተሠራ ነው።