የላሊበላን የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ለማቃለል እየተሠራ ነው።

3
ባሕር ዳር: ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት ውስጥ የውኃ ተቋማት አንዱ ነው።
በወቅቱ በደረሰው ጉዳት ውኃ ማቅረብ የማይቻልበት ደረጃ ደርሶ እንደነበር የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ኀይሉ ፈጠነ ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ በ2014 ዓ.ም ለከተማው ማኅበረሰብ በቦቲ ጭምር ውኃ የማቅረብ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ነው የገለጹት።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት ኮሚቴ እና ከጀርመን ኤምባሲ በተገኘ 2 ሚሊዮን ዩሮ 1 ሺህ 918 የሶላር ፓኔሎችን በማንጠፍ ከ2018 ኅዳር ጀምሮ የንጹህ መጠጥ ውኃ ማቅረብ ተችሏል።
ከሶላር የኀይል አማራጭ ባለፈ በኤሌክትሪክ እና በጀነሬተር ጭምር በመግፋት ማኅበረሰቡን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት።
በዚህም የከተማዋን የቀን የውኃ አቅርቦት ከዚህ በፊት ከነበረው 800 ሜትር ኪዩብ ወደ 1 ሺህ 300 ሜትር ኪዩብ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል። የሶላር የኀይል አማራጭ አገልግሎት ላይ መዋሉ የኤሌክትሪክ ኀይል ፍጆታ በግማሽ ቀንሷል።
በኀይል ችግር አገልግሎት አቁመው የነበሩ የፓንፖች በአዲስ እንዲቀየሩ እድል ፈጥሯል።
አሁን ላይ ከተማ አሥተዳደሩ ካለው ሕዝብ አኳያ በቀን 6 ሺህ 344 ሜትር ኪዩብ ውኃ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ምክትል ሥራ አሥኪያጁ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አምስት አዳዲስ ተጨማሪ የውኃ ጉድጓዶች ለመቆፈር የጥናት ሥራ መሠራቱን ነው የገለጹት።
የፕሮጀክቱን ዝርዝር የዲዛይን ሥራ ለመሥራትም ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር ውል ለመውሰድ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። የከተማዋን የውኃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ ያለውን ሥራ ረጅ ድርጅቶች እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
የላሊበላ ከተማ ነዋሪ የኾኑት ተጓዳ ደስታ ባለፉት ዓመታት በከተማዋ ባጋጠመው የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር በቦቲ ጭምር ውኃ ለማቅረብ ቢሞከርም ካለው የሕዝብ ብዛት አኳያ ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም እናቶች፣ አቅመ ደካሞች፣ ተማሪዎች ውኃ ለማግኘት ረጅም ርቀት ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር ገልጸውልናል። በውኃ ወለድ በሽታ ምክንያትም ለሕክምና ወጭ መጋለጣቸውን ገልጸውልናል።
በሶላር የኀይል አማራጭ የንጹህ መጠጥ ውኃ ማቅረብ ከተጀመረ ጀምሮ የተሻለ የውኃ አቅርቦት መኖሩን ገልጸዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ደባሽ ጌታመሳይ የሶላር የኀይል አማራጭ ከጀመረ ጀምሮ የተሻለ የውኃ አቅርቦት መኖሩን ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ በበዓላት ወቅት ያጋጥም የነበረው እጥረት መሻሻሉን ነው ያነሱት።
በቀጣይ የከተማዋን እድገት እና የቱሪዝም ፍሰት ታሳቢ ያደረገ ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየደሴ ከተማ አሥተዳደር በጥር ወር የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላትን በድምቀት ለማክበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አደረገ።