“ባልማር ኖሮ አረብ ሀገር የጉልበት ሠራተኛ ነበርኩ”

5

ባሕር ዳር: ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ1989 ዓ.ም በአማራ ክልል ድርቅ የተከሰተበት ወቅት ነበር፡፡ በልቶ ማደር ችግር ኾኖ ሕጻናት ከትምህርት ቤት ቀሩ፡፡

የሕጻን ማርዬ ቤተሰቦችም በድርቁ ምክንያት ልጃቸውን ማስተማር አቃታቸው፡፡ እናቱ በአንድ የችግኝ ጣቢያ የጉልበት ሥራ ለመቀጠር ከሕዝብ ጋር እየተጋፉ ነው፡፡ ማርዬ የእናቱን ቀሚስ ጨብጦ ከጉልበታቸው ሥር ድክ ድክ እያለ ደብተር እንዲገዙለት እና ትምህርት ቤት ለመሄድ ይማጸናል፡፡

ዕድለኛ ኾኖ በጉልበት ሥራው ከተቀጠሩ ደብተር ተገዝቶለት ትምህርት ቤት እንደሚሄድ እናቱ ቃል ገቡለት፡፡

በዚህ ሁኔታ ችግኝ ጣቢውያን የሚጎበኙ አንድ የክልል ኤክስፐርት የሕጻኑ ኹኔታ ሳባቸውና አቅርበው ጠየቁት፡፡ የ3ኛ ክፍል ጎበዝ ተማሪ መኾኑን ጠቅሶ የመማር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ተናገረ፡፡

እናቱ በሥራው ቢቀጠሩለት ትምህርቱን መቀጠል እንደሚችልም በኮልታፋ ግን በተስፋ አንደበት ገለጸ፡፡

የማርዬ እናት ደብተርና እስክርቢቶ ሊገዙለት የሚያስችላቸውን 50 ኪሎ ግራም ስንዴ እና ሦሥት ሊትር ዘይት በሚያስገኝላቸው ሥራ ተቀጠሩ፡፡

ማርዬ የሚወደውን ትምህርት ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ የዛኔው ትምህርት ወዳጁ ብላቴና፣ እንባውን በእናቱ ቀሚስ እየጠረገ ደብተር ካልተገዛልኝ ብሎ ያለቀሰው እና አንድ የክልል ኤክስፐርት ‘ከሰማይ የወረደለት’ ሕጻኑ ማርዬ ዛሬ ባለ ሦስተኛ ዲግሪ ነው፡፡

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የጥናት፣ የምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንትም ኾነዋል፡፡

ትምህርት ለሚፈልግ ሕጻን የተደረገ የያኔው ውለታ ዛሬ ሰው መሥራት መቀጠሉን ነው ዶክተር ማርዬ የሚናገሩት፡፡ ያ የክልል ኤክስፐርት ዛሬ ላይ የልማት ድርጅት የሚመሩ ዶክተር ኾነዋል፡፡

እንደኔ ላሉ ለበርካታ ችግረኛ ተማሪዎች ዕድላቸውን አቃንተዋልም ይላሉ፡፡ ያንን ታላቅ ሰው፣ ተፈጥሮ እና ትምህርትን ወዳጅ ምሁር ዶክተር ማርዬ አመሥግነው አይጨርሱም፡፡

ዶክተር ማርዬ ተምረው ያደጉበት ትምህርት ቤት በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ የሚገኘው ታገል ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡

ታገል የአሜሪካ የሕዋ ምርምር (ናሳ)ን ጨምሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የተሰማሩ በርካታ ምሁራንን ያፈራ ስመ ጥር ትምህርት ቤት ነው፡፡

ታገል አሁን ላይ የመማሪያ ሕንጻዎቹ ዘምመዋል፤ ምርጎቹ ተላልጠዋል፡፡ የቤተ መጻሕፍት እና ቤተ ሙከራ ክፍሎቹ ብቁ አይደሉም፡፡ ሌሎችም መፍትሄ የሚፈልጉ ችግሮች አሉበት፡፡

ይህንን ችግሩን የተረዱ የቀድሞ ተማሪዎቹ ተወያይተው ችግሮቹን ለይተዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም ንቅናቄ ጀምረዋል፡፡

እነ ዶክተር ማርዬም አስተምሮ ለደረጃ ላበቃቸው ትምህርት ቤት የበኩላቸውን ለማበርከት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ “አንድ ግለሰብ የትምህርትን ጠቀሜታ ተገንዝቦ እኔን ከደገፈኝ፤ እኔስ አስተምሮ ላሳደገኝ ታገል እንዴት አንሳለሁ?” ነው ያሉት፡፡

አቶ መሠረት በላይ በትምህርት ቤቱ ተምረዋል፡፡ የትምህርት ቤቱን መልሶ ግንባታም ያስተባብራሉ፡፡ የቀድሞ ተማሪዎች ከአካባቢው መሪ እና ሕዝብ ጋር ተወያይተናል፡፡ በአጭር ጊዜ ባለ ሁለት ፎቅ 15 የመማሪያ ክፍሎች መገንባት እና በረጅም ጊዜ ደግሞ ከጭቃ የተሠሩ ክፍሎችን ወደ ብሎኬት የመቀየር ዕቅዶች ይዘናል ብለዋል፡፡

ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሥራ መጀመራቸውን የጠቀሱት አቶ መሰረት 54 ሚሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ በሁለት ቀን ብቻ 600 ሺህ ብር ባንክ መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡

በተደረገው ውይይት ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች መነሳሳት መታየቱንም ገልጸዋል፡፡ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

የወገዳ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አስናቀው ቆየው በበኩላቸው የትምህርት ቤቱን ችግሮች ለመፍታት ከሦስት ዓመት በፊት ግንባታ መጀመሩን አስታውሰው በሰው ሠራሽ ችግሮች ተቋርጦ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ከተማ አሥተዳደሩ ሕዝቡን አስተባብሮ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ቆርጦ መነሳቱንም ገልጸዋል፡፡ የቀድሞ ተማሪዎቹም የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

እነ ዶክተር ማርዬ ትምህርት ቤቱን መልሶ ለመገንባት እና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የኮሚቴ አባል ኾነው እየሠሩ ነው፡፡ ባይተርፋቸውም አስተምሮ ሰው ላደረጋቸው ትምህርት ቤት ሳይኾኑ እንደማይቀሩ በሙሉ ተነሳሽነት እየተናገሩ ነው፡፡

ግጭት፣ የኑሮ ውድነት እና ተምሮ ሥራ ማጣት ቢኖሩ እንኳ ልጅን ከማስተማር ውጭ ሌላ ምን አማራጭ አለን? ሕጻናት እና ወጣቶች በቂ ዕውቀት ይዘው ሥራ ፈጣሪ እና ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ደግሞ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች መኖር ዋናው ቅድመ መስፈርት ነው፡፡ ጥራት ባለው ትምህርት ወጣቶችን በዕውቀት፣ በክህሎት እና በሥነ ምግባር የዘመኑን ውድድር እንዲሸንፉ እንደነዶክተር ማርዬ በቀና ልቦና “ላስተማረኝ ወገኔ ወረታውን መልሼ ለወገኔ” ማለትን ይጠይቃል፡፡

የገንዘብ እጥረቱ ይኖራል፡፡ መዋጮውም ይበዛ ይኾናል፡፡ ሌሎችም ስጋቶች ይኖራሉ ነገር ግን በችግሮችም ውስጥ ኾኖ ትውልዱን ማስተማር አማራጭ የሌለው የማኅበረሰብ ኀላፊነት ነው፡፡

ማኅበረሰቡ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ደግሞ ምሁራን እና የንግዱ ማኅበረሰብ ግንባር ቀደም መኾን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለዛሬው የማርዬ ዶክትሬት የማያውቃቸው የክልል ኤክስፐርት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ደጋግሞ ይናገራል፡፡ ያ የክልል ኤክስፐርት ለእናቱ የሥራ ዕድል ባይፈጥር ኖሮ ዛሬ ላይ አረብ ሀገር የቀን ሠራተኛ አለያም በከፋ ችግር ላይ ይገኙ እንደነበር ዶክተር ማርዬ ይናገራሉ፡፡

ዶክተር ማርዬ የማያውቀኝ ሰው ለመማሬ ትልቅ ውለታ ከሠራልኝ ለማውቀው ትምህርት ቤቴ ለታገልማ ምንም ባደርግ ሲያንስ ነው ባይ ናቸው፡፡

ዘጋቢ፦ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መይሳው የሚሉት አንድ ሰው ነበረ አንድ ኾኖ ተወልዶ ሺህ ኾኖ የኖረ”
Next articleየደሴ ከተማ አሥተዳደር በጥር ወር የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላትን በድምቀት ለማክበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አደረገ።