
ባሕር ዳር: ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፈተና ዘመን የተፈጠረ፣ በፈተና ውስጥ ለሀገሩ የኖረ፤ ኢትዮጵያን ከአንድ ምዕራፍ ወደሌላ ምዕራፍ ያሸጋገረ፣ የመከፋፈልን ዘመን ያስቀረ፤ አንድነትን እንደ አለት ያጠነከረ ጀግና ነው።
ለኢትዮጵያ ሲል ልጅነቱን ሰጥቷል፤ ለኢትዮጵያ ሲል ደስታውን ትቷል፤ ለኢትዮጵያ ሲል በረሃ ወርዷል፤ ደጋ ወጥቷል፤ ለኢትዮጵያ ሲል በባዶ እግሩ ተንከራትቷል፤ ለኢትዮጵያ ሲል ከጠላቶቿ ጋር ተናንቋል፤ ለኢትዮጵያ ሲል እንደ ንጉሥ ሳይኾን እንደ አሽከር ኾኗል፤ ለኢትዮጵያ ሲል ሕይዎቱን ሰጥቷል።
ኢትዮጵያን እስከ ሞት ድረስ ወደዳት፤ እስከ መቃብር ድረስ አፈቀራት፤ በትውልድ ልብ ላይ ቀረጻት፤ ቃል ኪዳኑን አተመባት ንጉሠ ነገሥት አጼ ቴዎድሮስ።
እርሱ የአንድነት አባት፣ የኢትዮጵያዊነት ምልክት ነው። እርሱ ከዘመን የቀደመ፤ ትናንት ላይ ኾኖ ዛሬ ላይ የቆመ ባለራዕይ ነው። እርሱ ኢትዮጵያን ከልቡ ያፈቀረ፤ እርሱ ለሕልሙ የኖረ፤ ለራዕዩ የታተረ፤ ከዘመኑ የቀደመ፤ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር እጹብ ያሰኘ ሥልጣኔን የጀመረ ጥበበኛ ነው መይሳው።
ጳውሎስ ኞኞ አጤ ቴዎድሮስ በተሰኘው መጽሐፋቸው
ቴዎድሮስ በመሳፍንት የተከፋፋለች ሀገሩን ለማንሳት የተነሳ ታላቅ ሀገር ወዳድ ነበር ሲሉ አትተዋል። ቴዎድሮስ በብዙ ገዢዎች ተቆራርጣ የነበረችውን ኢትዮጵያ እንደነበረችበት አንድ ለማድረግ ከፍተኛ ድካም ደክሟል። ያለ እረፍት ሠርቷል ሲሉም አስፍረዋል።
ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከተለያዩ መኳንንት አገዛዝ አውጥቶ ባንድ መንግሥት ሥር እንድትተዳደር ለማድረግ የጥርጊያውን መንገድ የከፈተ ዋናው መሐንዲስ ነው ። ለአጤ ዮሐንስ እና ለአጤ ምኒልክ መጓዣውን መንገድ በሕይወቱ የክፈተ ነው ብለው ጽፈዋል።
ተክለ ጻድቅ መኩሪያ አጼ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት በተሰኘው መጽሐፋቸው ቴዎድሮስ የዘመነ መሳፍንትን የቋጨ አንድነትን ያመጣ ብርቱ ሰው ነው። እርሱ ያስቀመጠው የብሔራዊ አንድነት የመሠረት ደንጋይ የማዕዘን ራስ ኾኖ ለነ አጼ ዮሐንስ እና ለአጼ ምኒልክ የአሥተዳደር ዘመን ጥርጊያ ጎዳና በመክፈት አገልግሏል ይላሉ።
ተክለጻድቅ ሲጽፉ “አፄ ቴዎድሮስ በዘመነ መንግሥታቸው በታላቅ የቤተ መንግሥት ሕንጻ ባማረ አዳራሽ ተቀምጠው ዘውድ ደፍተው፤ በትረ መንግሥት ጨብጠው፤ በዙፋን ላይ ተንሠራፍተው፤ በወርቅ አልጋ እና በሚደላ ፍራሽ ላይ ተጋድመው፤ የዚህን ዓለም ንጉሣዊ አዱኛ ማጣጣም ሳያምራቸው ለራሳቸው ባርኔጣ ለእግራቸው ጫማ ሳይፈልጉ፤ ያለምንም ዕረፍት እና መዝናናት በድንኳን እየኖሩ በከብት ጀርባ እና በእግራቸው ከአውራጃ ወደ አውራጃ በመዘዋወር ዳገት ቁልቁለቱን ሸለቆ እና ወንዛ ወንዙን በማቋረጥ፤ ቆንጥር ለቆንጥር በክረምት እና በበጋ በመንከራተት የታገሉ እንደነበሩ አንስተዋል።
ጉልበታቸውንም ኾነ አዕምሯቸውን፤ በመጨረሻ ሕይወታቸውንም ሙሉ በሙሉ ለሚወዷት ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የሥልጣኔ እና የአንድነት ሕይወት ሠውተዋል ነው ያሉት። የኢትዮጵያን አንድነት እና ውሕደት የሚወድ የአሁኑም፣ የወደፊቱም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይኸን ውለታ ተገንዝቦ የእኒህን ንጉሥ ስማቸውን በአክብሮት እና በአድናቆት ሊዘከረው ይገባል” ብለው ጽፈዋል።
ፊሊፕ ማርስዲን የጻፉት እና ብሩክ መኮንን የተረጎሙት የቴዎድሮስ ዕዳ አንዲት ኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ቴዎድሮስ በበርካታ ተግባራት የተፈተነ፤ ጥበበኛ፣ ሌሊትም ኾነ ቀን በሙሉ ኃይሉ ለሀገር እድገት ለመሥራት የቆረጠ፤ ሃሳብ እና ዓላማውን ግልጽ እና አጭር በኾነ መንገድ የሚገልጽ፤ ድብቅነት የማይታይበት ስብዕና ያለው መሪ ነው ተብሎም ተመዝግቧል።
አቤ ጉበኛ አጼ ቴዎድሮስን “ለሀገራቸው ተፈጥረው፤ ለሀገራቸው ኖረው፤ ለሀገራቸው ምቾታቸውንም፤ ሕይወታቸውንም የሰው ገናና ንጉሥ ናቸው” ብለውታል። ቴዎድሮስ በታሪክ የገነነ ስም እንዳለው ሲጽፉ “ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ የታሪክ መድረክ ላይ ያንፈራጥጣሉ። ቴዎድሮስ ገና ገና ወደፊት በሚመጣው የኢትዮጵያ ትውልድ ልብ ውስጥ እንደ እንቁ ያበራሉ ብለው ጽፈዋል።
ቴዎድሮስ የአንድ ዘመን ትውልድ ንጉሥ ብቻ አይደለም። የዚያ ዘመን ከዚያ ዘመን ተከትሎ የመጣው ዘመን፤ የአሁኑ ዘመን እና የሚመጣው ዘመን ትውልድ ነው እንጂ፤ የዛሬውን እና የወደፊቱን የኢትዮጵያ ትውልድም በመንፈስ ይገዛዋል ተብሎ በታሪክ ሠፍሯል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በቴዎድሮስ ዓይነት ተነሥቶ፣ በቴዎድሮስ ዓይነት ሠርቶ፣ በቴዎድሮስ ዓይነት ያለፈ ታላቅ ሰው ቀድሞት ያልተፈጠረ፤ ለሀገሩ የመጀመሪያውና እርሱ ብቻ የሆነው ሀገሩን አፍቃሪ ብለው ጽፈዋል አቤ ጉበኛ።
አቤ ጉበኛ በቴዎድሮስ ጀግንነት ሁሉም ተስማምቶ መስክሮለት ከሙግቱ ወጥቷል፤ ካሳ ፍርሃት ጨርሶ የሌለበት ጀግንነት እና የጦርነት ስልት ወዳጆቹም ጠላቶቹም እንዲያደንቁት እና እንዲያጨበጭቡለት ያደረገ ነው ሲል ጽፏል።
አጼ ቴዎድሮስ የሚመራው ሕዝብ ሳይፈጠርለት የተፈጠረ ታላቅ መሪ፤ የሀገሬን ሕዝብ ታላቅ፣ ባለጸጋ፣ በሰላም የሚኖር፤ የሠለጠነ አድርጌ ለማየት እችላለሁ ብሎ ሌት ተቀን ሲዋትት የኖረ ነው።
ይህ ጀግና ሰው የተወለደው ከ207 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ጥር 06/1811ዓ.ም በጎንደር ቋራ ነበር። ይህ አንድ ለእናቱ የተባለ ጀግና ሀገሩን በጀግንነት እና በጽናት ያገለገለ ነው ብለዋል።
“መይሳው የሚሉት አንድ ሰው ነበረ፤
አንድ ኾኖ ተወልዶ ሺህ ኾኖ የኖረ” እንደተባለ ያ ቋረኛ ጀግና አንድ ኾኖ ተፈጥሮ እንደ ሺህ የኖረ፤ እንደሺህ የሠራ፤ የሺህ ዘመን ታሪክ ያኖረ ጥበበኛ እና ባለ ራዕይ ነው።
“እመቴ አትጠገብ ምነዋ መንፈግሽ
አንድ ብቻ ወልደሽ ይበቃል ማለትሽ”
ቴዎድሮስ ሁሉም እናቶች መንታ ኾኖ በተፈጠረ ብለው የሚመኙለት፤ እናቱ እንደ ቴዎድሮስ አይነት ልጅ ደጋግማ እንድትወልድ የሚመኙለት ጀግና ነው።
ለሀገር የተወለደክ፣ ለሀገርም የኖርክ፣ ለሀገርም ያለፍክ ነህና ታሪክህ በትውልድ ይነገራል፤ በትውልድ መከካል የነገሥከው ታላቁ ንጉሥ ኾይ እንኳን ተወለድክ።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
