
“ጣሊያን ብሎ ነበር ኢትዮጵያን ሀገሬ
እምቢ አለ እንጂ ኮስትር ተጠምዶ እንደበሬ”
ባሕር ዳር: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገሩን ከራሱ አስቀደማት፤ ከሕይወቱም በላይ ወደዳት፣ ከአብራኩ ክፋይ አስበለጣት፣ ሀገሩን ከግራ ጎኑ አስቀዳማት፣ ሀገሩን ከወገን ዘመዶቹ አላቃት፣ ኢትዮጵያን በመከራ ውስጥ ኾኖ አፈቀራት፣ ለፍቅሯ ግለት በዱር በገደል ተመላለሰላት፣ በበረሃ ተንከራተተላት፣ ወንድም ገበረላት፣ ወዳጅ ዘመድ ሰጣት፣ የመከራውን ጽዋ ተጎነጨላት፤ ኢትዮጵያን እስከሞት ወደዳት፣ ከአንቺ በላይ የማስቀድመው የለኝም ብሎ ማለላት፤ የመሃላውን ቃልም ጠበቃት፤ ቃሉን አከበራት።
ኮልታፋ አንደበቷን እየሰማ ያሳደጋት፣ በእቅፉ ውስጥ አድርጎ የልጅነት ማዕዛዋን ያሸተታት፣ እየዳበሰ ልጄ ወዳጄ ያላት፣ ግንባሯን እየሳመ ታቲ ዝግራ ያጫወታት፣ እሾህ እንዳይወጋት፣ እንቅፋት እንዳይመታት የሳሳላት የሻሽወርቅን ትቶ ኢትዮጵያን አስቀደማት።
ልጁን ከአንጀቱ ይወዳታል፣ ከዐይኑ ስትርቅ ይናፍቃታል፤ ከኢትዮጵያ ግን አላስበለጣትም፣ ኢትዮጵያን በልጁ አልተካትም፣ ሀገሩን በየሻሽወርቅ ለቅሶ ተክዞ ለጠላት አሳልፎ አልሰጣትም፡፡ የአባትነት ልቡን አበርትቶ፣ የሻሽወርቅን ትቶ ከሀገሩ ጠላቶች ጋር ተናነቀ እንጂ፡፡
በልጅ እና በእናት ሀገር ፍቅር ተፈተነ፡፡ ፈተናው ከባድ ነው፣ ልጅ እና እናት ሀገር ለምርጫ ቀርበዋልና፡፡

” እንዳሻችሁ አርጓት ቃሌ አይለወጥም
ምን ቢያንገበግበኝ ፍቅሯ እንደ ውኃ ጥም
ብሎ አለፈ በላይ ልጅ ከሀገር አይበልጥም” እንዳለ ከያኒው በላይ ልጅ ከሀገር አይበልጥም። ሀገርን በልጅ አይለወጥም ብሎ ኢትዮጵያን አስቀደመ፡፡
እረኞች በላይ በላይ እያሉ አዜሙለት፣ ባለቅኔዎች አባ ኮስትር እያሉ ተቀኙለት፡፡ እርሱ የተመላለሰባቸው ጋራ እና ሸንተረሮች፣ እርሱ ውጊያ የገጠመባቸው ምሽጎች አንደበት ቢኖራቸው በላይ በላይ ባሉ ነበር፡፡ ጠመንጃውን አንግቶ፣ ዝናሩን ሞልቶ፣ አፈሙዝ ወልውሎ፣ ሳንጃውን ስሎ ሲወጣ ሀገሩ ጉድ ይላል፤ ሁሉም በላይ በላይ ይላል፡፡
በዓድዋ ተራራ ላይ ዘመን የማይሽረው በትር ያረፈባት ኢጣሊያ የጣለችውን ክብሯን፣ ያጠፋችውን ስሟን መልሳ የምታነሳበት ዘመን ትጠብቅ ነበር፡፡ በዓለም አደባባይ ያሳፈረቻትን ኢትዮጵያን ያለ በቀል ማለፍ አልተዋጠላትም፡፡ በዓድዋ ላይ የደረሰባትን ተደጋጋሚ ሽንፈት የምታካክስበት ሌላ ዕድል መሞከር አስፈለጋት እንጂ፡፡
ኢትዮጵያን በክንዳቸው ደፍጥጠው እንዲያስገብሩ የተላኩት ወታደሮቿ ሁሉ በኢትዮጵያውያን መዳፍ ተጨብጠው ቀርተዋል፡፡ በሮም አደባባይ ፎክረው የተነሱት በዓድዋ ተራራ ላይ እንዳልነበር ኾነዋልና ለበቀል ተነሳች።
ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ክንድ በዓድዋ ተራራ ላይ የደቀቀ እና የወደቀ ስሟን ታነሳ ዘንድ አርባ ዓመታትን ተሰናዳች፡፡ መሰናዶዋንም እንደጨረሰች ወደ ኢትዮጵያ ገሰገሰች፡፡ የዓድዋው ጀግና ምኒልክ አልፈው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመንበሩ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ መጣች። በዚያን ጊዜ ጀግኖች ኢትዮጵያን ለሀገሬ ብለው ተነሱ።
በረሃ በመውረድ ፣ ከጠላት ጋር ተዋደቁ ፡፡ የኢጣሊያ ዘመናዊ መሳሪያ አስግቷቸው ሀገራቸውን አሳልፈው አልሰጡም፡፡ ሀገርን ለጠላት አሳልፎ መስጠት በኢትዮጵያውያን ዘንድ አይታወቅምና፡፡ ለኢትዮጵያውያን ክብራቸውም፤ ታሪካቸውም ኢትዮጵያን መጠበቅ እና ማስጠበቅ ነውና።
ጀግኖች አርበኞች በየአቅጣጫው እየተነሱ ጠላትን መውጫ መግቢያ፣ ማለፊያ ማግደሚያ አሳጡት፡፡ በዚህ ዘመን በአርበኝነት ጠላትን ከቀጡ ጀግኖች መካከል ደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ አባኮስትር ይነሳል፡፡ የበላይ አፈሙዝ የጠላትን ግንባር እየለየች መትታለች፣ የበላይ ጥይት ከጠላት ገላ እየተሰካች እልፍ ጠላትን ጥላለች፡፡

በላይ እንኳን በጦርነት በሰላምም ጊዜ ለሰላምታ ነጭ እጄን አይጨብጣትም የሚል ኩሩ ጀግና ነው፡፡ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር እነሆ ጀግና በሚለው መጽሐፋቸው ጄኔራል ሳንፎርድ የተባለ አንድ የእንግሊዝ መኮንን ለሰላምታ የበላይን እጅ ሊጨብጥ ሲዘረጋ በላይ ዘለቀ ʺለፈረንጅ እጄን አልሰጥም” አለው ብለዋል፡፡
እኔ የዘለቀ ልጅ እያለ ሲነሳ ጠላት ነብር እንዳየ ፍየል የሚበረግግለት፤ ፍርሃት በልቡ ያልፈጠረበት ጀግና ለሀገሩ መከበር ያለ ድካም ከጠላት ጋር ተናንቋል፡፡
አበራ ጀምበሬ አባኮስትር በተሰኘው መጽሐፋቸው በላይ ለሀገሩ አንድነት፣ ነጻነት እና ሉዓላዊነት አያሌ ጀብዱዎችን የፈጸመ፤ በጀግንነት የጸና ጀግና መኾኑን ጽፈዋል።
አባ ኮስትር በላይ ልጁ የሻሽወርቅ በጠላት ተይዛ፣ ባለቤቱ አልፋ፣ የእርሱን ዘመዶች ቤት እያቃጠሉበት እርሱ ግን ወደ ኋላ ሳይመለስ ይዋጋ ነበር፡፡ ጽናት፣ ጀግንነት እና ዕምነት ከእርሱ ጋር ነበሩ፡፡ ጦርነቱ ከቀናት እስከ ወራትም አልነበረም ለዓመታት ነው እንጂ፡፡ ለዓመታት በዘለቀው ጦር በላይ በጽናት የጠላት ግንባርን እየለየ መታ፡፡

የበላይ ዘለቀን ስሜት የሚነኩ አሳዛኝ ክስተቶች ተፈጥረዋል፣ በሸበል በረንታ የኢጣሊያ ወታደሮች ሕጻናትን እና ሴቶችን በግፍ ገድለዋል፤ ይሄን ሁሉ ያደረጉት በላይ ትግሉን እንዲያቆም ነበር፤ በላይ ግን የበለጠ ጸና፣ የበለጠ ጠነከረ እንጂ ነፍጡን አልዘቀዘቀም፡፡
ጣሊያኖች የሻሽወርቅን እንስጥህ እና ለእኛ እደር ብለውት ነበር፤ በላይ ግን ልጅም የሚኖረው በክብርም የሚኖረው ሀገር ሲኖር ብቻ ነው በማለት አሻፈረኝ አላቸው።
ʺበላይ አባ ኮስትር በላይ አባ ነፍሶ፣
በረንታ ላይ ጣለው ለምጨን ላይ ተኩሶ” እየተባለ የተገጠመለት ጀግና ተመልከት እያለ ጠላትን በየዱር ገደሉ የሚጥል፣ የጠላትን መሪ ከተመሪው ጋር በጥይት ብሎ የሚነጥል ነው፡፡ የትኛውም ችግር ቢመጣ ተቋቁሞ የሀገር ፍቅር ማጽናትን፤ በጽናት፣ በጀግንነት፣ በውሳኔ ሰጭነት መቆምን በላይ ያስተምራል። በላይ መከራውን ተቋቁሞ ለሀገር ዋጋ የከፈለ ጀግና ነውና፡፡
ሀገሩን የሚወድ ሁሉ ከበላይ ዘለቀ ታሪክ መማር ግድ ይለዋል። የትኛውም ፈታኝ ሁኔታ እና ችግር ቢገጥም ከግለሰብ ችግር ይልቅ የሀገርን ችግር ማስቀደም፣ ለሀገር እና ለሕዝብ ችግር ዋጋ መክፈል ሀገሩን ከሚወድ ዜጋ ይጠበቃልና።
ʺመኳንንቱ ሁሉ እየተጨነቀ፣
ለምጨን ካፋፉ ላይ ያው በላይ ዘለቀ፤
መኳንንቱ ሁሉ ዕምነቱን ሲያወልቀው፣
አባ ኮስትር በላይ አለ እንዳጠለቀው” እየተባለ የተገጠመለት በላይ ለሀገሩ ለገባት ቃል ኪዳን የኖረ፣ በሀገር ፍቅር የታሰረ ጀግና ነው፡፡
“ጣሊያን ብሎ ነበር ኢትዮጵያን ሀገሬ
እምቢ አለ እንጂ ኮስትር ተጠምዶ እንደበሬ” እንደተባለ
በላይ አባ ኮስትር የኢጣሊያንን ሠራዊት እንደ ረመጥ ጠብሶ ሀገርን ነጻ አድርጓል፣ የሕዝብን ነጻነትም አስከብሯል፡፡
ዳሩ ከነጻነት ማግሥት በላይ ረጅም ዘመን አልቆዬም፡፡ ከንጉሣዊ ሥርዓቱ ጋር አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ ጎልማሳው በላይ ሮጦ ያልጠገበባትን፣ በእሳት ተፈትኖ ጀብዱ የሠራበትን፣ በሕይወቱ ተወራርዶ ነጻ ያደረጋትን ኢትዮጵያ ተሰናበታት፡፡ በላይ ከእነውነቱ፣ በላይ ከእነ ጀግንነቱ፣ በላይ ከእነ ነጻነቱ፣ በላይ ከእነ ልበ ሙሉነቱ ሳይጎድል ምድርን የተሰናበታት ልክ በዛሬዋ ቀን ጥር 5/1937 ዓ.ም ነበር፡፡

“ፈሪ እና ተራራ ዘላለም ይኖራል
ጀግና ብርሌ ቶሎ ይሰበራል” እንዳለ የሀገሬው ሰው
የጀግና ዕድሜው ረጅም አይደለም። ጀግና ታሪኩ ነው ረጅም እና ዘላለም። ጀግና ሰው በአጭር ጊዜ ዘመን የማይሽረው ታሪክ ይጽፋል ፡፡ በላይን የፈጠረው የቀደመው የአባቶች ጀግንነት ነውና በአጭር ጊዜ የረዘመ ታሪክ ጽፏል፡፡
በምድር አጭር ዕድሜ የኖረው አባ ኮስትር ዘመን ተሸጋሪ ታሪክ ሠርቷል፣ ሀገርን በብርቱ ትግል በነጻነት አቆይቷል፣ ስሙን ከመቃብር በላይ ትቷል፡፡
አባኮስትር ለሀገር ክብር ተዋድቀሃል፣ ለሀገር ክብር በዱር በገደል ተንከራትተሃል፤ በልጅ ፍቅር ተቃጥለሃል፤ በመከራ ዘመን ጸንተሃል፤ ኢትዮጵያ በተጣራች ጊዜ ቀድመህ ወጥተሃልና ኢትዮጵያ ታመሠግንሃለች፤ ሀገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያንም በላይ በላይ ይሉሃል፤ በስምህ ይምሉብሃል፤ ታሪክህን እየጠበቁ ለትውልድ ያስተላልፉልሃል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
