ኮሌራን በዘላቂነት ለመከላከል የንጽህና መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ያስፈልጋል።

5

 

ባሕር ዳር: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከሃይማኖት መሪዎች እና አጋር አካላት ጋር መክሯል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስሜነህ አያሌው እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ዓመታት ኮሌራን ለመከላከል ሰፊ ጥረቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

ኮሌራን በዘላቂነት ለመከላከል የንጽህና መሠረተ ልማቶችን ማሟላት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በጸበል ቦታዎች የውኃ አቅርቦት፣ የመጸዳጃ ቤቶች እና ሌሎችንም የንጽህና መጠበቂያ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ለዚህም በየደረጃው ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ታዬ የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኩልም በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።

በቀጣይም ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል በጸበል ቦታዎች የአካባቢን እና የግል ንጽህና አጠባበቅ አሠራሮችን እንዲተገበሩ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀዋል።

የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አዕላፍ አባ ኃይለማርያም ትንሳኤ ኮሌራን ጨምሮ ተላላፊ በሽታዎች ጊዜ የማይሰጡ ናቸው ብለዋል። ምዕመናን በሚበዙበት እና ንጽህናቸው ባልተጠበቁ ቦታዎች የሚስፋፉ ስለመኾናቸውም አንስተዋል።

በሀገረ ስብከቱ የጸበል ቦታዎችን ጽዱ እንዲኾኑ በእቅድ ተይዞ እየተከናወነ ስለመኾኑ ጠቁመዋል። የመጠጥ እና የንጽሕና መጠበቂያ የሚኾን የውኃ አቅርቦት፣ የመጸዳጃ ቤቶችን ማሟላት፣ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

በምክክር መርሐ ግብሩ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ኮሌራን ለመከላከል በጋራ ቃል ገብተዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአራጣ እና የሕግ ተጠያቂነት
Next article“ጣሊያን ብሎ ነበር ኢትዮጵያን ሀገሬ እምቢ አለ እንጂ ኮስትር ተጠምዶ እንደበሬ”