አራጣ እና የሕግ ተጠያቂነት

20

ባሕር ዳር: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አራጣ ተበዳሪን ያልተገባ የወለድ ስሌት በማስከፈል የሚፈጸም የወንጀል ድርጊት ነው፡፡ አበዳሪ በሚወስነው መሠረት ከዓይነቱ በተጨማሪ የሚከፈል ክፍያም ነው፡፡

ስለ አራጣ ምንነት፣ ጉዳቶችና በሕግ ስለመከልከሉ በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀሎች ጉዳዮች ዳይሬክተር ሙሉጌታ አሻግሬ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡

በከፍተኛ የወለድ መጠን የሚሰጥ የአራጣ ብድር የምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ጉዳቶች ያስከትላል፡፡

ጉዳቱን ለመከላከልም በሕግ ከተወሰነው የወለድ ምጣኔ በላይ ገንዘብ ማበደር ወንጀል ኾኖ ተደንግጓል፡፡

👉የአራጣ ብድር ጉዳቶች

ተበዳሪዎች ያላቸውን ሃብት ወይም በብድሩ ሠርተው የሚያገኙትን ትርፍ አበዳሪው ስለሚወስደው ለኪሳራ ይዳረጋሉ፡፡

የአራጣ ብድር ባንኮች ላይ የሚቀመጥ እና ለኢንቨስትመንት ብድር የሚኾን ተቀማጭ ገንዘብን ይቀንሳል።

በአራጣ ብድር የሚዘዋወርን ገንዘብ መንግሥት ስለማያውቀው ከምጣኔ ሃብቱ የሚሠበሠብ ገንዘብ አይኖርም፤ በመኾኑም የሕዝብ ደኅንነት የሚያናጋም የወንጀል ተግባር ነው።

👉የአራጣ ማበደር የወንጀል ተጠያቂነት

የአራጣ ብድር በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 712 እና 715 እንዲሁም ፈቃድ ሳይይዙ የባንክ ሥራ መሥራትን አስመልክቶ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 592/2000 አንቀጽ 2፣ 3/1/ እና 58/1/ እንዲሁም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 መሠረት ያስጠይቃል።

በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አራጣ ወንጀል ኾኖ ተደንግጓል፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 712 የአራጣን ወንጀልነት ሲገልጽ “ማንም ሰው በሕግ ከተፈቀደው ወለድ በላይ ገንዘብ ያበደረው እንደኾነ ወይም ካበደረው ገንዘብ ጋር በግልጽ ተመጣጣኝ ያልኾነውን ንብረት በምትኩ እንዲሰጠው ያደረገው ወይም ቃል ያስገባው እንደኾነ በቀላል እሥራት ወይም እንደነገሩ ኹኔታ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና መቀጮ ይቀጣል” በማለት ይደነግጋል።

የተበዳሪውን የገንዘብ ችግር፣ የግንዛቤ ደረጃ እና የመደራደር አቅም የሚያሳጡ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶችን በመጠቀም በሕግ ከተፈቀደው የወለድ ምጣኔ በላይ ለመቀበል ማበደር እና ካበደረው ገንዘብ ጋር በግልጽ ተመጣጣኝነት የሌለውን ንብረት በምትኩ እንዲሰጠው ያደረገ ወይም ቃል ያስገባ በቀላል እሥራት ወይም እንደነገሩ ኹኔታ ከአምሥት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት መቀጮ ይቀጣል።

በፍታብሔር ሕጉ አንቀጽ 2ሺህ 479 መሠረት የወለድ ምጣኔ፡-
-ተዋዋዮች በወለድ የሚከፈለውን ገንዘብ በዓመት ከ12 በመቶ በላይ እንዲኾን መዋል አይችሉም፤

-በወለድ የሚከፈለው ገንዘብ ከ12 በመቶ በላይ በዓመት እንዲኾን በጽሑፍ የተደረገ ውል ቢኖር እንኳን ተበዳሪው በዓመት ዘጠኝ በመቶ ብቻ ወለድ መክፈል አለበት፡፡

-እንዲሁም በፍታብሔር ሕግ አንቀጽ 2ሺህ 478 ላይ ተበዳሪው ወለድ እንዲከፍል የውል ቃል ከሌለ በቀር ላበዳሪው ወለድ መክፈል እንደሌለበት ይደነግጋል፡፡

በብድር ውል ተዋዋይ ወገኖች ከዋናው ገንዘብ በተጨማሪ ወለድ እንዲኖር አስቀድመው መዋዋል እንደማይችሉ የፍትሐብሄር ሕጉ ቁጥር 2ሺህ 481 (1) ያመለክታል።

በዚህ የሕግ ድንጋጌ መሠረት በብድር ውል ግንኙነት ላይ የወለድ ወለድ በሕግ የተከለከለ ነው።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍትሕ ሥርዓቱን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next articleኮሌራን በዘላቂነት ለመከላከል የንጽህና መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ያስፈልጋል።