የፍትሕ ሥርዓቱን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው።

9
ገንዳ ውኃ: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው ለማድረግ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት አሊ መሐመድ አገልግሎት አሰጣጡ ፍትሐዊ የኾነ እና የተሻለ ነው ብሏል።
ከተለያዩ ተቋማት የሚላኩ መረጃዎች እና ማስረጃዎች ትክክለኛነታቸው ተጣርቶ ፍትሐዊ በኾነ መንገድ ውሳኔ እንዲሰጣቸውም ጠይቋል።
ሌላኛዋ ተሳታፊ ወይዘሮ እህትነሽ መዝገቡ የፍርድ አገልግሎት አሰጣጡ በተሻለ መንገድ ግልጸኝነት እና ሀቀኝነት የተሞላበት ይኾን ዘንድ መረጃዎች በዘመናዊ መንገድ የታገዙ እንዲኾኑ ጠይቀዋል።
በከሳሽ እና በተከሳሽ መካከል ያሉ ጉዳዮችን ፍርድ ቤቱ በቶሎ አይቶ ውሳኔ ባለመሰጠቱ ባለጉዳዮች ለከፍተኛ ወጭ እየተዳረጉ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የመተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የወንጀል ዳኛ መስፍን አሰጋ በግማሽ ዓመቱ በፍትሐ ብሔር ጉዳዮችነክ ከ1 ሺህ 30 በላይ መዝገብ ቀርቦ ከ850 በላይ መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በወንጀል ነክ ጉዳዮች ደግሞ ከ610 በላይ መዝገብ ቀርቦ ከ580 በላይ መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን አብራርተዋል።
የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ለዳኞች እና ለባለሙያዎች አጫጭር ሥልጠና እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተሰጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ኢብራሄም የሱፍ እንደተናገሩት የፍርድ ቤቶችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እና ቀልጣፋ ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በተያዘው ዓመት እንደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፋይሎችን ወደ ዲጂታል በመቀየር ዳኞች ባሉበት ውሳኔ የሚሰጡበት ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በተቻለ መጠን ከሌሎች ተቋማት የሚላኩ መረጃዎችን ትክክለኛ እና ግልጸኝነት ያላቸው እንዲኾኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ አስረድተዋል።
ተቋሙ የዲጂታላይዜሽን አሠራርን በመከተል ለይግባኝ ወደ ሌላ ቦታ ይላኩ የነበሩትን ተገልጋዮች የማስቀረት ሥራ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአዲሱ የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?
Next articleአራጣ እና የሕግ ተጠያቂነት