ባሕር ዳር: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በ6ኛ ዙር፤ 5ኛ ዓመት፤ 11ኛ መደበኛ ጉባኤው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ማሻሻያ አዋጅን አጽድቋል፡፡
በገጠር መሬት ቢሮ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና ካዳስተር ዳይሬክተር ታከለ ሃብቴ ስለ አዲሱ የመሬት አዋጅ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አዋጁ የቀድሞውን የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 252/2009ን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ነው፡፡
አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት ላለፉት 10 ዓመታት የተከሰቱ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ለውጦችን ታሳቢ አድርጓል፡፡
የሕዝቡን የአገልግሎት ፍላጎት፣ የቴክኖሎጂውን ማደግ፣ የገጠር መሬትን አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሳይንሳዊ የማድረግን አስፈላጊነት፣ በአተገባበር ሂደት የታዩ ጉድለቶችን ለማስተካከል እና ዘላቂ የገጠር መሬት አሥተዳደር መረጃን ለማዳበር ነው፡፡
ከሀገራዊ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ 1324/2016 ጋር ተመሳሳይ የኾነ የመሬት አሥተዳደር እንዲኖራቸው ለማድረግ ታሳቢ መደረጉንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
በአዋጁ የተሻሻሉ እና የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች፡-

ለሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች እና ነጋዴዎች በገጠር መሬት የመጠቀም መብት ሰጥቷል።

መሬትን ስለመለካት፣ ካርታ ስለማዘጋጀት፣ እንዲሁም ከዳታ ጋር በተያያዘ አሻሚ የነበሩ ሕጎችን እና በማንዋል ብቻ የነበረውን የመሬት አሥተዳደርን በዲጂታልም እንዲቻል አድርጓል።

ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መብት እና ጥቅም በማካተት ብሎም በማጠናከር ለጉዳዩ ባለቤት ሰጥቷል።

የፍትሐብሔር እና የወንጀል ተጠያቂነትን በማጠናከር በተናጠል የእሥራት እና የገንዘብ መቀጮን አስቀምጧል።

ለባሕላዊ ሽምግልና እና የግጭት መፍቻ መንገዶች ዕውቅናም ሰጥቷል።

ለዲጂታል ዳታ ቤዝ የመሬት መረጃ ዕውቅና ሰጥቷል።

በገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሥርዓቱ የተፈጠረ መረጃ መሠረታዊ ስህተት እንዳለበት እስካልተረጋገጠ ድረስ ለትክክለኛ መረጃነቱ ዕውቅና ሰጥቷል።

በከተማ እና በገጠር አካባቢ የሚለያይ ኾኖ በመሬቱ ላይ ቤት እና ቋሚ ተክሎች ያለማ ባለመሬት በመሬቱ ላይ የለማን ንብረት የመሸጥ መብትም ፈቅዷል።
የመሬት አዋጁ በአዲስ ያመጣቸው መብቶች እና ዕድሎች፦

መሬትን ለብድር ማስያዣነት መጠቀም፤ ብድሩን መክፈል ካልቻለም የመሬት መጠቀሚያ መብቱ ሊወሰድ ይችላል።

አርሶ አደሮች መሬታቸውን በከፊልም ኾነ በሙሉ ለሌላ አካል ማከራየት ይችላሉ።

የመሬት መጠቀሚያ መብቱን እንደ ካፒታል በመቁጠር ከባለሃብቶች ጋር በሽርክና ማልማት ይቻላል።

ለእርሻ፣ ለግጦሽ ወይም ለደን ልማት ተብሎ የተለየን መሬት ለታቀደለት ዓላማ ብቻ ለማዋል ያስገድዳል።

የመሬት መጠቀሚያ መብትን ለቤተሰብ አባል በስጦታ ወይም በኑዛዜ የማስተላለፍ መብትንም ሰጥቷል።

መሬትን እንደ ኢኮኖሚያዊ አቅም በመጠቀም ወደ ዘመናዊ ግብርና ለመሸጋገር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ተገልጿል፡፡
አዋጁን ለማስፈጸም ደንብ እና መመሪያ በቀጣይ እንደሚወጣም ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት፡፡