በአማራ ክልል የመማሪያ መጻሕፍት ሥርጭት በምን ደረጃ ላይ ነው ?

5
ባሕር ዳር: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ እና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የግብዓት አቅርቦት የማሟላት ሥራ ይሠራል።
ከግብዓት አቅርቦቶቹ መካከል የመማሪያ መጻሕፍት ሥርጭት ይገኝበታል። በክልሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍት እየታተሙ ለተማሪዎች ይሠራጫሉ። ነገር ግን እስካሁን ድረስ መጻሕፍትን ለተማሪዎች ለየብቻ ማዳረስ አልተቻለም።
በባሕርዳር ከተማ የሽንብጥ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት የመጻሕፍት እጥረት መኖሩን ተማሪዎች እና መምህራን ተናግረዋል። በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 86 ተማሪዎች መታጨቅም የመማር ማስተማር ሂደቱን ክፉኛ እየጎዳው መኾኑን ተማሪዎች እና መምህራን ገልጸዋል።
👉የተማሪዎች እና የመምህራን ቅሬታ፦
የ7ኛ ክፍል ተማሪዋ ብሌን ባንተይርጋ የመጻሕፍት እጥረት ስላለባት መምህራን የሚሰጡትን አጭር ማስታወሻ ብቻ ለመጠቀም መገደዷን ገልጻለች። ይህም በውጤቷ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግራለች። የክፍል መጨናነቅ ለሙቀት እና ለጫጫታ መንስኤ መኾኑንም አንስታለች።
የ8ኛ ክፍል የጀኔራል ሳይንስ መምህር ዜናው መንግሥቱ በሒሳብ፣ በሳይንስ እና በእንግሊዝኛ ትምህርቶች አንድ መጽሐፍ ለአምስት ተማሪዎች እየተጋራ መኾኑን ጠቁመዋል።
በአንጻሩ የስፖርት እና የስነ ጥበብ መጻሕፍት ከተማሪው ቁጥር በላይ ተርፈው መከማቸታቸውን ገልጸዋል።
👉የትምህርት ቤቱ ምላሽ፦
በሽንብጥ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር ጋሻው ጥሩነህ እንደሚሉት የሚታተሙ መጻሕፍት ከተማሪው ቁጥር ጋር አይመጣጠኑም።
ችግሩን ለመቅረፍ በአይሲቲ (ICT) ክፍል መጻሕፍት ማስቀመጥ እና የሶፍት ኮፒ አማራጮችን መጠቀም ቢሞከርም፣ የክፍል ጥምርታው ግን አሁንም አሳሳቢ ነው ብለዋል።
👉የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምላሽ፦
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክተር ይገርማል አያሌው ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የመጻሕፍት እጥረት የለም ብለዋል።
ችግሩ የተፈጠረው ከተለያዩ አካባቢዎች በፈለሱ ተማሪዎች ምክንያት የተማሪ ቁጥር ከዕቅድ በላይ በመጨመሩ እና በማከፋፈል ሂደት መኾኑን ገልጸዋል።
ለክልሉ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን መጻሕፍት ታትመው ወደ ሀገር እየገቡ በመኾኑ በቅርቡ እንደሚሰራጩ እና ችግሩን እንደሚፈቱ ተናግረዋል።
የክፍል ጥበቱ ወቅታዊ ችግር በመኾኑ አሁን ላይ አዲስ ግንባታ ማካሄድ አዋጭ እንዳልኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጥምቀትን በጎንደር ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleአዲሱ የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?