
ጎንደር: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው መግለጫ ሰጥተዋል።
ከንተባው ወርኃ ጥር ጎንደር ከተማ የምትሞሸርበት፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ጎልተው የሚወጡበት መኾኑን ተናግረዋል።
የከተሞች እናት የኾነችው ጎንደር ከተማ የሃይማኖት መቻቻል፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ መቻቻል እና መከባበር ማዕከል መኾኗን አስረድተው ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ከ2 ሚሊዮን በላይ እንግዶች ወደ ጎንደር እንደሚገቡ አሳውቀው በአካባቢው ባሕል እና ወግ ለመቀበል እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።
በዓሉን ለመታደም አሁን ላይ እንግዶች መግባት መጀመራቸውንም አሳውቀዋል።
የእንግዶቹ ምቾት ለመጠበቅ ከተማ አሥተዳደሩ ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ማመቻቸቱን ተናግረዋል። የሆቴል እና መሰል አገልግሎቶች ከወዲሁ መጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል።
የዘንድሮን የጥምቀት በዓል ልዩ የሚያደርገው የፋሲል አብያተ መንግሥታት ተጠግነው ለአዲስ እይታ መብቃታቸው እና የከተማዋ ልማት ለማረጋገጥ የኮሪደር ሥራ ተግባራዊ መደረጉ መኾኑን ተናግረዋል።
አብያተ መንግሥታቱን መጎብኘት ለሚፈልጉ እንግዶች የምሽት የጉብኝት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።
የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ሕይወት በአብያተ መንግሥታት የሚያሳይ መርሐ ግብር መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
ከተማዋ እምቅ የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንት እና የልማት አቅም እንዳላት የተናገሩት አቶ ቻላቸው ያለውን ዘርፈ ብዙ ሃብት ተጠቅመው ማልማት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች 500 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ሀይሉ ማሞ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
