ንግድ ባንክ ወልድያ ዲስትሪክት አነስተኛ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች ብድር ለማቅረብ ስምምነት ላይ ደርሷል።

3
ወልድያ: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወልድያ ዲስትሪክት ከወልድያ ከተማ አሥተዳደር እና ከሰሜን ወሎ ዞን ጋር አነስተኛ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች ብድር ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።
የባንኩ የሪቴይል ባንኪንግ ክፍል ሥራ አስኪያጅ ኤልያስ ይልማ አነስተኛ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ታስቦ ብድሩ መመቻቸቱን ነው የገለጹት።
በመጀመሪያ ዙር ብድር በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ እስከ 20 ሺህ አርሶ አደሮችን የብድር ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
ብድሩ ለአጭር እና ለመካከለኛ ጊዜ ብድር ይሰጣል ያሉት ኀላፊው በሥራ ማስኬጃ ዘርፍ እንደ የእንስሳት መኖ ምርት፣ የእንስሳት ርባታ፣ አትክልትና አበባ ምርት እንዲሁም ሜካናይዜሽንን ያካትታል ነው ያሉት።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ደስታ ሞላ ለከተማው የኑሮ ውድነትን ለማርገብ እና የገበያ ፍላጎትን ለማርካት መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል።
ብድሩ ቦታው ኖሯቸው በገንዘብ እጥረት የተቀመጡ አርሶ አደሮችን በማነቃቃት ምርትን በማሳደግ ገበያን የማረጋጋት ሥራ ለመሥራት ያስችላል ነው ያሉት።
ከተማ አሥተዳደሩ ከያዘው የከተማ ግብርና እቅድ አኳያም የብድር አቅርቦቱ ደጋፊ ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊዋ በተለይም በዶሮ እና ሌሎች እንሳሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ተግባራትን ለማጠናከር ብድሩ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ተገኝ አባተ በበኩላቸው አርሶ አደሮችን ከበሬ በማላቀቅ የእርሻ ሜካናይዜሽን ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት።
ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር ባሻገር የብልጽግና ፓርቲ ኢኒሼቲቭ የኾነውን የሌማት ትሩፋት መሬት ላይ ወርዶ ለመሥራት የሚያስችል ተጨማሪ አቅም ይፈጥል ሲሉ አስረድተዋል።
በተለይም በአሳ ሃብት፣ በወተት ተዋፅኦ እና በማድለብ የዞኑን አቅም አሟጦ ለመጠቀም ባንኩ የሚያቀርበው ብድር አጋዥ ነው ብለዋል።
መምሪያው በመዋቅሩ በኩል አርሶ አደሮችን የማንቃት ተከታታይ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሴፍትኔት መርሐግብር የነዋሪዎችን ኑሮ እያሻሻለ ነው።
Next articleመንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ከብልሹ አሠራር የፀዳ ለማድረግ ዲጂታል የግዥ ሥርዓትን ተግባራዊ አድርጓል።