
ፍኖተሰላም: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፍኖተሰላም ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ስጦታ ገብረ ሚካኤል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ኑሯቸውን ሲገፉ መቆየታቸውን ነግረውናል ። አሁን ላይ ግን በሴፍትኔት መርሐግብር በመሳተፍ የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በከተማ ግብርና በመሥራትም ከራሳቸው አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች የጓሮ አትክልት ውጤቶችን እያቀረቡ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የሴፍትኔት ተጠቃሚ ጌታነህ ነጋ ከሳምንት ሦሥት ቀናት በከተማ ጽዳት እንደሚሠሩ ገልጸውልናል።
በሌሎች ቀሪ ቀናት ግን በአትክልት ልማት በመሳተፍ ገቢያቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ የሥራ እና የቁጠባ ባሕላቸውን እንዳሳደገላቸው አብራርተዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ከ932 በላይ የሴፍትኔት መርሐግብር ተጠቃሚዎች መኖራቸውን የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደደር የምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ባለሙያ ተስፋዬ ሞላ ገልጸዋል።
ከአጠቃላይ ተጠቃሚዎች ውስጥ 279 አባላት ከከተማ ጽዳት በተጨማሪ ከአምስት ሄክታር በላይ መሬት ላይ በበጋ መስኖ እያለሙ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በዚህም የኑሮ ሁኔታቸውን እንዲያሻሽሉ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። በሚያከናውኗቸው የልማት እና የጽዳት ተግባራት ውጤታማ እንዲኾኑ የሕይወት ክህሎት እና የንግድ ዕቅድ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
