ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ምን እየተሠራ ነው?

7
‎ባሕር ዳር: ጥር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የ2018 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት የማጠቃለያ ፈተና ጊዜ ደርሷል።
ለመሆኑ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?
‎‌በጎንደር ከተማ የመሠረት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ አምሳል ዋናቸው ለማጠቃለያ እና ለክልል አቀፍ ፈተና በቡድን በማጥናት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገች መኾኑን ተናግራለች። መምህራንም የተመረጡ የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጧቸው እንደኾነ ገልጻለች።
‎‌የስምንተኛ ክፍል ተማሪው ገብረሥላሴ ታዬ ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም እና የማጠናከሪያ ትምህርቱን በመከታተል ለተሻለ ውጤት እየተዘጋጀ መኾኑን ነግሮናል። ቤተ መጻሕፍት ሁሉንም ቀናት ለአገልግሎት ክፍት ኾነው እየተጠቀሙ መኾኑን ነው የተናገረው።
‎‌የመሠረት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ስጦታው አምኃ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ከወላጆች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
ተጨማሪ የሰው ኀይል በመቅጠር ተማሪዎች በፈለጉት ጊዜ እንዲጠቀሙ በሁሉም ቀናት ቤተ መጻሕፍቱ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ገልጸዋል።
‎‌ከመደበኛው የትምህርት ጊዜ ውጭ የተመረጡ የትምህርት አይነቶች እና በተመረጡ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ነው። የመለማመጃ ጥያቄዎች ተዘጋጅተው ተማሪዎች ራሳቸውን እንዲፈትሹ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለው የመጽሐፍ ጥምርታ የተሻለ እንደኾነ ተናግረዋል። ‌ለተማሪዎች ውጤታማነት መምህራን፣ ወላጆች እና ተማሪዎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
‎‌የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስንታየሁ ነጋሽ በዚህ ዓመት መመዝገብ ከነበረባቸው ተማሪዎች 92 በመቶ መመዝገባቸውን አስታውሰዋል፡፡
ያለፈውን ዓመት የክልል አቀፍ ፈተና ውጤት መሠረት በማድረግ ለተማሪዎች ውጤታማነት ለመምህራን አጫጭር ሥልጠናዎች መሰጠቱንም ገልጸዋል።
ተማሪዎች እርስ በእርሳቸው እንዲማማሩ እና በተለይም በሳይንስ ትምህርት ብቁ እንዳኾኑ ቤተ ሙከራዎችን እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው፤ በክበባት ለትምህርታቸው አጋዥ የኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
‎‌ተማሪዎችን በሥነ ልቦና ለማዘጋጀት የምክር አገልግሎት በመስጠት እና በተከታታይ ምዘና ክፍተታቸውን ለመሙላት ጥረት ስለመደረጉም አንስተዋል።
ከወላጆች ጋር በመወያየት ተማሪዎች እንዲበቁ በትብብር ስለመሠራቱ እና ተማሪዎች በራሳቸው ውጤት ላይ ኀላፊነት እንዲወስዱ ጥረቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ለሥራዎች መተግበር በየሳምንቱ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ነውም ብለዋል።
‎በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክተር ይገርማል አያሌው ተማሪዎችን ውጤታማ እንዲኾኑ ለማስቻል ከመደበኛው የመማር ማስተማር ትግበራ በተጨማሪ አሠራሮች ተቀምጠዋል ብለዋል፡፡
ሁሉንም ቀናት የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት መስጠት፣ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት እና ለተማሪዎች የሥነ ልቦና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግን ጠቅሰዋል፡፡
‎በገጠሩ አካባቢ የአዳር ጥናት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ መብራት እንዲያገኙ፣ ማኅበረሰቡ በሚያደርገው ድጋፍ የምግብ አገልግሎት እያገኙ እና እንዲያጠኑ መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም 48 ትምህርት ቤቶች ላይ ተጀምሮ 1ሺህ 386 ተማሪዎች ተጠቃሚ ኾነዋል፤ አፈጻጸሙም በየሳምንቱ ክትትል እንደሚደረግ ጠቅሰዋል፡፡
‎የክልል አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች 50 በመቶ በላይ አምጥተው ከክፍል ክፍል እንዲዛወሩ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
ተማሪዎች፣ ወላጆች መምህራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየነገ ሀገር ተረካቢ ብቁ ዜጋን ለማፍራት የተማሪዎች ምገባ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
Next articleሴቶች ከአባልነት ባለፈ በውሳኔ ሰጭነት አቅም ስፍራን እንዲይዙ እየተሠራ ነው።