
ደብረ ብርሃን: ጥር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን እና ደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ስር በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች በዛሬው ዕለት የተሐድሶ ሥልጠና ጀምረዋል።
የክልል እና የዞኑ ከፍተኛ መሪዎች፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ትጥቃቸውን አስረክበዋል።
በግጭቱ ምክንያት ሕዝባችን ተንቀሳቅሶ እንዳይሠራ ኾኗል ያለው በከሰም ክፍለ ጦር ኀይለ ማርያም ማሞ ብርጌድ የአሥተዳደር ኀላፊ የነበረው አርቲስት ሙሉቀን መስፍን ከዚህ በላይ መቆየት አማራን ሕዝብ ስር ወደ ሰደደ ችግር ማስገባት ነው ብሏል።
ሌላኛው ከምንጃር ሸንኮራ ነበልባል ብርጌድ ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ የነበረው ሃምሳ አለቃ ፈለቀ ሰርጤ ግጭቱ የአማራ አርሶ አደሮች የግብርና ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ስላልቻሉ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስነናል ብሏል፡፡
ታጣቂዎቹ የበደሉትን ሕዝባቸውን ለመካስ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ጫካ ያሉ ወንድሞችም እጃቸውን ለሰላም እንዲዘረጉ እና የአማራን ሕዝብ ክብር በሚመጥን መንገድ መታገል እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥታችሁ በሠለጠነ መንገድ ለመታገል በመምጣታችሁ እኛም የማቋቋም ኀላፊነታችንን በአግባቡ እንወጣለን ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለሚያደሙ ኀይሎች ሰላማዊ ምላሽ ሰጥታችኋል ያሉት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ ናቸው፡፡
የእናንተ ወደ ሰላም መምጣት ቤተሰብን ከብተና፣ አካባቢን ከፀጥታ ችግር የሚታደግ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት ሰላምን መርጠው ለመጡ ታጣቂዎች የመንግሥት ኀላፊነት ጭምር ወስደው እየሠሩ በመኾናቸው በመንግሥት ላይ እምነት ሊኖር ይገባል ብለዋል።
ጥያቄ እና ፍላጎት በመገዳደል ሳይኾን በሠለጠነ መንገድ ነው የሚመለሰው ያሉት የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ ከዚህ በኋላ ግጭትን በቃ ማለት የሁሉም ድርሻ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
በጫካ የገቡ ታጣቂዎች ሕዝብ እና መንግሥትን የበደሉ ቢኾንም ሰላም ይበጃል ብለው በመምጣታቸው በክልል ደረጃ በርካታ ታጣቂዎች ወደ ሕዝብ ተቀላቅለዋል ብለዋል።
በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል አበባው ሰይድ በበኩላቸው ታጣቂዎቹ ለሰላም ዋጋ ሰጥተው በመምጣታቸው አመስግነው እስካሁን የበደላችሁትን ሕዝብ ለመካስ መዘጋጀት አለባችሁ ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
