
ባሕር ዳር: ጥር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ በመኳቢያ እና ጎብጎብ ቀጣና በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው ገብተዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉትን ታጣቂዎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የጸጥታ ኃይሎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሰላም አማራጭን ተቀብለው የገቡ ታጣቂዎች
ተሰልፈው የቆዩበት የትግል መስመር የተሳሳተ እና ሕዝብን ያጎሳቆለ መኾኑን ተናግረዋል። ይህን በመረዳት የቀረበውን የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ ለተደረገላቸዉ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል። ሌሎች ታጣቂዎችም የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት
የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ክፈተዉ በትጥቅ ትግል የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ እና የተሰለፋቹሁበት መገድ የተሳሳተ መኾኑን በመረዳት የሠላም አማራጭ መቀበላቹህ ብልህነት ነው ብለዋል።
የሰላምን አማራጭ ተቀብለው በመግባታቸውም ምስጋና አቅርበዋል። ሰላም ለሁሉም ዜጎች አስፈላጊ ነው ያሉት ኀላፊው አሁንም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች የሰላምን አማራጭ በመቀበል ችግሮችን በንግግር በመፍታት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ከላይ ጋይንት ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የሀሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ፈትተን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ አለብንም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
