የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር

8
ባሕር ዳር: ጥር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በጠላት ወረራ ዘመን በዚህ ሳምንት ጥር 01/1931 ዓ.ም የተመሠረተ ድርጅት ነው፡።
አባላቱ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ የትግል ዘመን እነዚያ ወጣት ኢትዮጵያውያን አንጀታቸውን ለረሀብ፤ እግራቸውን ለሾህ እና ለጠጠር፤ ግንባራቸውን ለጥይት አጋልጠው ሀገራቸውን የጠበቁ ጀግኖች ናቸው፡፡
እነዚህ ጀግኖች ሞትም ቢመጣ እናት ሀገራቸውን አሳልፈው ለጠላት ላለመስጠት፤ ነጻነታቸውን ለጊዜያዊ ሹመት ብሎም ለሽልማት ላለመለወጥ ችግሮችን የተጋፈጡ ጀግኖች ናቸው።
ደጃዝማች ከበደ ተሰማ “የታሪክ ማስታወሻ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ይህ ማኅበር በአርበኝነት ዘመን በሸዋ ክፍለ ሀገር በ1931 ዓ.ም «የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማኅበር» በሚል ስም ተሰይሞ የተቋቋመ ማኅበር እንደነበር አስፍረዋል፡፡
✍️የደብረ ማርቆስ ከተማ መሥራች የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት እረፍት
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት እና አድዋ ትልቅ ቁርኝት አላቸው። ንጉስ ተክለ ሃይማኖት የጎጃም ጦርን ይዘው ወደ አድዋ በመዝመት የድሉ አንድ አካል የነበሩ ጀግናም ናቸው፡፡
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጎጃም ገዥ በመኾን ደብረ ማርቆስን በመመስረት ስማቸው ጎልቶ የሚነሳ ባለታሪክም ናቸው።
የኢትዮጵያ ታሪክ ከተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ ገጽ 263 ላይ እንደሚያትተው ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ራስ እያሉ ጀምሮ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ሁለት ታላላቅ ዘመቻዎችን አድርገዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የሱዳን ደርቡሾች ድንበር ተሻግረው 100 ሺህ የሚኾን ሠራዊታቸውን ይዘው በመሄድ ድል አድርገዋል፡፡
ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት በር በከፈተው ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ወቅትም የጎጃምን ጦር በመምራት 3ሺህ ሠራዊት ይዘው በመዝመት ታላቅ ድል አስመዝግበዋል፡፡
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በዘመናቸው የተሻለ ነው ብለው ያሰቡትን ነገር ለራሳቸው እና ለሀገራቸው ሲፈጽሙ ኑረው በዚህ ሳምንት ጥር 3/1893 ዓ.ም ደብረ ወርቅ ላይ አርፈዋል፡፡
✍️የሊግ ኦፍ ኔሽን ምሥረታ
የያኔው ሊግ ኦፍ ኔሽን የዛሬው የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ተልዕኮ የዓለምን ሰላም ማስጠበቅ በሚል የተመሠረተ ነበር። የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ድርጅትም ነው።
ድርጅቱ የተመሠረተው ጥር 02/1920 በፓሪስ ሲኾን የመጀመሪያውን የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ ሰላምን ለማምጣት ሲባል የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡
ሊግ ኦፍ ኔሽን ወይንም በአሁኑ አጠራሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘመናዊው ዓለም አቀፋዊ አሥተዳደር አብነት እንደመኾኑ ዘመናዊውን ዓለም በጥልቅ ቀርጿልም ይባልለታል።
ይህ ድርጅት በሚጠበቅበት ደረጃ በዓለም ላይ ባሉ ኃያላን ሀገራት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እና ጦርነቶች እንዲቆሙ ማድረግ ባይችልም የዓለም ሰላም እንዲረጋገጥ ግን ጥረት ማድረጉ ነው የሚገለጸው፡፡
የመረጃ ምንጫችን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረ ገጽ ነው።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ጠንካራ የፖለቲካና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ተሠርተዋል”
Next articleበትጥቅ ላይ የቆዩ አካላት ወደ ሰላም መግባታቸውን ቀጥለዋል።