
ባሕር ዳር: ጥር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ በስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ መክሯል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ በርካታ የፖለቲካ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
ክልሉ ችግር ውስጥ የቆየ በመኾኑ ይህንኑ መሠረት በማድረግ እና ከችግሩ ለመውጣት የሚያስችል ጠንካራ የፖለቲካ እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል። እነዚህም ውጤት አምጥተዋል ነው ያሉት። ይህንን ተከትሎም በርካታ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን በመከተል ወደ የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል ብለዋል።
ከመሪዎች ጀምሮ እስከ ሕዝቡ የደረሰ በአካባቢያዊ፣ በክልላዊ፣ በሀገራዊ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መጠነ ሰፊ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንም መስጠት ተችሏል ነው ያሉት። በዚህም ከመላው ሕዝብ ጋር መግባባት ላይ መድረስ እንደተቻለ አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኀላፊ ዲባ ጉቱ ባለፉት ስድስት ወራት በዋናው ጽሕፈት ቤት የሚወርዱ ሰነዶችን እና አቅጣጫዎችን መሠረት በማድረግ ሰፊ የአቅም ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን እና ልማትን ለማስቀጠል ከአጎራባች ክልሎች ጋር በትብብር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥርን የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውንም አንስተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ይሁን አሰፋ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ የሕዝብ ንቅናቄ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ፣ የገዥ ትርክትን የሚያጠናክሩ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ የአቅም ግንባታ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት። በዚህም አበረታች ውጤቶችን ማምጣት እንደተቻለ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
