
እንጅባራ፡ ጥር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር የመጀመሪያው ምዕራፍ የ1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ተጀምሯል።
የኮሪደር ልማቱ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች ፣ የመንገድ ዳር ማረፊያዎች፣ ስማርት የኤሌክትሪክ ፖሎች ተከላ፣ አረንጓዴ ልማት፣ የጎርፍ ማፈሻሻ ልማትና የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች ልማት የተካተቱበት ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የኮሪደር ልማቱ የከተማውን ውበት በመጨመር የቱሪስት ፍሰትን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱን በአከባቢው ካሉ የቱሪዝም ሃብቶች ጋር ተመጋጋቢ እንዲኾኑ በማድረግ የከተማዋን ተመራጭነት ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የእንጅባራ ከተማ ሕዝብ ከግል ጥቅሙ ይልቅ የጋራ ጥቅምን የሚያስቀድም የልማት አርበኛ ነው ብለዋል።
የከተማዋ ሕዝብ የኮሪደር ልማት የሚነካቸውን ንብረቶች ያለምንም ካሳ እና ትክ ቦታ በማፍረስ ለከተማው ልማት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ እንደኾነም አንስተዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተሞችን የወደፊት የእድገት ጉዞ ታሳቢ ያደረጉ መኾን ይገባቸዋልም ነው ያሉት።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳደሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገፅታ በማሻሻል የንግድ እና ኢንቨስትመንት እድሎችን ለማስፋት ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ከሕዝብ ለሕዝብ የሚለማ ፕሮጀክት ነው ያሉት አቶ አይተነው ኅብረተሰቡ ለሥራው ስኬታማነት የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ የኮሪደር ልማቱ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን የሚያሰፋ፣ የትራንስፖርት ፍስሰትን የሚያሳልጥ እና የሥራ እድል ፈጠራን የሚጨምር መኾኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የተጀመረው የ1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት በከተማዋ ለመገንባት ከታቀደው 5 ኪሎ ሜትር ውስጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ መኾኑንም ገልጸዋል።
ግንባታውን በሁለት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ይሠራል ነው ያሉት።
የከተማው ነዋሪዎችም ለከተማቸው ልማት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
