የደን ጭፍጨፋ ሳይፈፀም መከላከል እና ጥፋት ሲፈፀምም መጠየቅ ይገባል።

8

ወልድያ: ጥር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ከደን ጠባቂዎች፣ ከእድር መሪዎች፣ ከቀበሌ አሥተዳዳሪዎች፣ ከግብርና ባለሙያዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የአካባቢውን ደን እና የተፈጥሮ ሃብት መጠበቅ ላይ ያተኮረ ምክክር አካሂዷል።

የከተማ አሥተዳደሩ ደን ጠባቂዎች እና የአካባቢ ሽማግሌዎች ተራቁቶ የነበረው አካባቢያቸው በደን እየተሸፈነ የገቢ ምንጭ እየኾናቸው መኾኑን ገልጸዋል።

የአካባቢያቸው ደን ለእንስሳት መኖ ምንጭ፣ ለንብ እርባታ እና ለአፈር ለምነት ጥበቃ እያገለገላቸው መኾኑንም ተናግረዋል።

ወቅታዊውን የጸጥታ ችግር ምክንያት በማድረግ ሕገወጦች እየሠሩ ያለውን የደን ጭፍጨፋ በጋራ እንደሚከላከሉም ጠቁመዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ደስታ ሞላ በአራት ቀበሌዎች 2ሺህ 604 ሄክታር የደን ሽፋን መኖሩን ገልጸዋል።

በዚህም እንስሳት በማድለብ እና በንብ እርባታ ከ300 በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል አንደተፈጠረም አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ወቅታዊ የጸጥታ ችግሩን ምክንያት በማድረግ የደን ምንጠራ እና ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ነው ብለዋል። የደን ጭፍጨፋ የፈፀሙ 51 ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ ተደርጎ 28 ገለሰቦች ውሳኔ እንዲያገኙ ኾኗል ነው ያሉት።

የወልድያ ከተማ ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ ሰማየ ፈለቀ በደን ጭፍጨፋ ወንጀል ክስ እየተመሠረተ ሕጋዊ ርምጃ እየተወሰደ መኾኑን ገልጸዋል።

የደን ጭፍጨፋ ሳይፈፀም መከላከል እና ጥፋት ሲፈፀምም ለሕግ አካላት አሳልፎ መስጠት፣ ማስረጃ ኾኖ በመቅረብ አንደማኅበረሰብ የድርሻን መወጣት ይገባል ብለዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ንጉሥ ዝናቡ የደን ሃብትን መጠበቅ የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅ ባሻገር የኢኮኖሚ ምንጭ ኾኗል ነው ያሉት።

ይህን ሃብት ማልማት እና መጠበቅ የማኅበረሰቡ ኀላፊነት መኾኑንም አስገንዝበዋል።

በተለይም እድሮች እና የቀበሌ መዋቅሮች የማኅበረሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ጉዟችን ተጠናክሮ ይቀጥላል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየእንጅባራ ከተማን የኮሪደር ልማት በአከባቢው ካሉ የመስህብ ሃብቶች ጋር ማስተሳሰር ይገባል።