
ባሕር ዳር: ጥር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራን አስጀምረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባጋረ መረጃ ኢትዮጵያ እምቅ አቅሟን እና ታላቅ ርዕይዋን የሚመጥን ሌላ ተጨማሪ ሜጋ ፕሮጀክት ጀምራለች ብሏል።
የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ይኾናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመኾን የአውሮፕላን ማረፊያውን ግንባታ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እለቱ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊነት እና ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ አንድ እጥፋት ነው በማለት ገልጸውታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም የሀገር የኩራት ምንጭ መኾኑን አንስተዋል። ይኽ የኾነው ግን ያለተግዳሮት በመጓዙ ሳይኾን በጽናት በተሞላው እንቅፋቶችን የመሻገር አቅሙ እና በአፍሪካ የፋና ወጊነት ሚናው የተነሳ መኾኑን ገልጠዋል። የአየር መንገዱ ትልቁ ጥንካሬ የሚመነጨው ከጠንካራው ተቋማዊ ባሕሉ የሚመነጭ መኾኑን አንስተዋል። ይኽም በሚከተሉት ላይ የተገነባ መኾኑን ገልጸዋል:-
– ለጥንቃቄ እና ደኅንነት ቅድሚያ መሥጠት
– በፈጠራ እና ጠንካራ ሥራ የሚመራ መሪ
– ከ26 ሺህ 000 በላይ ቁጥር ያለው በአየር መንገዱ ሰንደቅ ተሸካሚነት እና የሚወክለውን የሚያምኑ እና የሚያከብሩ ሠራተኞች
– ያላሰለሰ የመማር እና የአቅም ግንባታ ጥረት
ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎሜትር ርቀት በ1910 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ቢሾፍቱ ለአውሮፕላኖች የተመቸ ከባቢ ብሎም ኢትዮጵያን መዳረሻ ለሚያደርጉም ኾነ ለትራንዚት መንገደኞች ምቹ አቀባበል የተመቸች ያደርጋታል። ፕሮጀክቱ ብዛት ያላቸው የተሽከርካሪ መስመሮችን የያዘ አዲስ አበባን ከአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ የሚያገናኝ ዘመናዊ መንገድ ግንባታን ያካተተ ነው። በሰዓት ከ120 እስከ 200 ኪሎሜትሮች ፍጥነት ያለው የከፍተኛ ፍጥነት የባቡር ሀዲድ እና ሥርዓት ግንባታንም አካትቷል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ የሚችል ነው። በታቀደው መሠረት ሙሉ ግንባታው በሚጠናቀቅበት ወቅትም በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተናግዳል። ይኽም ኢትዮጵያን ከዓለም ግንባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት ማዕከላት አንዷ ያደርጋታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
