“ሕዝቡ የሚፈልገው ሰላምን፣ አብሮነትን፣ አንድነትን እና ኢትዮጵያዊነትን ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

9

ባሕርዳር: ጥር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ እየመከረ ነው።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ አማራ ክልል ወደ ቀደመ ሰላሙ እየመጣ ነው ብለዋል። ይህንን አስቻይ የሰላም ሁኔታ ለማምጣት መስዋዕትነት ተከፍሏል ነው ያሉት። በዚህም ክልሉ የተረጋጋ የሰላም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ሕዝቡ በርካታ በደል እና መከራ ደርሶበታል ያሉት ኀላፊው ሕዝቡ የሚፈልገው ሰላምን፣ አብሮነትን፣ አንድነትን እና ኢትዮጵያዊነትን ነው ብለዋል። ጠርዝ የያዘ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ እንደማይፈልግ በተግባር እያሳየ መኾኑን ገልጸዋል።

በክልሉ አስተማማኝ ሰላምን በማምጣት ለምርጫ ሥራዎች አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) ብልጽግና ፓርቲ በሀሳብ ልዕልና የሚያምን ፓርቲ ነው ብለዋል። ማንኛውም ልዩነት በውይይት እና በሀሳብ የበላይነት መፈታት እንዳለበት አስቦ የሚሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ፓርቲ ነው፤ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልዕልናን ለማረጋገጥ እየሠራ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ተሰሚነቷ የጨመረ እና የተከበረች እንድትኾን አስቀድሞ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከልመና እና ከተረጅነት እንድትላቀቅ በሁሉም ክልሎች ሰፊ ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል። የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ እሳቤን የሚከተለው ብልጽግና ፓርቲ በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጅ አጠቃቀም እና በሌሎችም ዘርፎች እምርታዊ ለውጦችን አምጥቷል ፤ በቀጣይም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።

ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ ባሻሻለችው የጤና ፖሊሲ በርካታ ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው።
Next articleኢትዮጵያ እምቅ አቅሟን እና ታላቅ ርዕይዋን የሚመጥን ሌላ ተጨማሪ ሜጋ ፕሮጀክት ጀምራለች።