
ደሴ: ጥር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደሴ ዲስትሪክት እና የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር በግል እና በቡድን ለተደራጁ አርሶ አደሮች የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዳ ብድር ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደሴ ዲስትሪክት ሪቴል ባንኪንግ ሥራ አሥኪያጅ መብራቱ ሞላ ግብርናን ለማዘመን እና ምርታማነትን ለማሳደግ በሰብል ልማት፣ በወተት፣ በፍራፍሬ እና ግብርና ማሽነሪን ጨምሮ በስድስት ምርቶች ላይ ባንኩ ለአርሶ አደሮች ብድር ለመስጠት ተዘጋጀቷል ብለዋል፡፡

በብድር አገልግቱ አነስተኛ የመሬት ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች፣ የሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች፣ ዩኒየን ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ሌሎች የብድር አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚኾኑም ገልጸዋል።
የባንኩ ደንበኛ መኾን፣ የመሬት የይዞታ ማረጋገጫ መያዝ እና ሌሎች የብድር መስፈርቶችን በማሟላት አርሶ አደሮች የዕድሉ ተጠቃሚ መኾን ይችላሉ ነው የተባለው።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን አርሶ አደሮች ከተለመደው አሠራር ወጥተው ግብርናን ለማዘመን በትራክተር፣ በኮምባይነር እና ሌሎች የግብርና ምርት ማሳደጊያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
እስከአሁን የነበረውን የፋይናንስ ጉድለት ለመሙላት ከንግድ ባንክ ጋር ስመምነት መደረሱ ለዞኑ አርሶ አደሮች ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የእንስሳት ሃብትን ለማዘመን ዝርያ ለማሻሻል፣ ለእንስሳት ጤና እና መኖ አቅርቦት፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ላይ የሚስተዋለውን የፋይናንስ አቅርቦት ለመቅረፍ የብድር ስምምነቱ ፋይዳው የጎላ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በአተገባበር ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን እየፈቱ ለመሄድ ሁሉም ተቋማት ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
