“የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ይኾናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

11

ባሕር ዳር: ጥር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራ አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የኢትዮጰያን ፈጣን የአየር ትራንስፖርት እድገት እና እየሰፋ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለምአቀፍ ትስስር ዘላቂ ለማድረግ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ መንገደኞችን በዓመት የማስተናገድ አቅሙ ላይ ከደረሰው ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተጨማሪ አዲስ ሜጋ ጣቢያ እየለማ ይገኛል ብለዋል።

ይኽ የተለያዩ አውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የወደፊቷ የአፍሪካ ግምባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት በር የማድረግ አላማን ያነገበ መኾኑን ገልጸዋል።

የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ይኾናል። ይኽም ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የኢንደስትሪ ማስፋፊያ አጀንዳ እና የረጅም ዘመን የአቪየሽን ስትራቴጂ ጋር የተናበበ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ያጠናክራል። በAfCFTA ማሕቀፍ የአፍሪካን የማገናኘት አቅም ይጨምራል። የንግድ እና ቱሪዝም ኮሪደሮችን ያሰፋል። ኢትዮጵያንም ቀዳሚ የበይነ አህጉር ማዕከል ያደርጋታል ነው ያሉት።

ከአዲስ አበባ ደቡብ ምሥራቅ 40 ኪሎሜትር አካባቢ የምትገኘውና 1910 ሜትር ከፍታ ያላት ቢሾፍቱ ለአውሮፕላኖች ሥራ የተመቸ ከባቢ ያላት መኾኗን ገልጸዋል። መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ ላደረጉም ኾነ ለትራንዚት መንገደኞች ብቁ ሁኔታ ያላት ናት ብለዋል።

ለመዲናችን ያላት ቅርበት ከነባሩ የአየር ትራንስፖርት ምኅዳር ጋር በቀላሉ የተዋሃደ አሠራር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። የመጀመሪያው ምዕራፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሥራ በዓመት 60 ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግድ ነው። ሲጠናቀቅም አፍሪካን ከዓለም ቀዳሚ የአየር ትራንስፖርት መነኻሪያዎች አንዷ የሚያደርጋትን በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ላይ ይደርሳል ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየእስቴ – ስማዳ መንገድ ግንባታ ዋና ዋና ሥራዎች ተጠናቀቁ።
Next articleከንግድ ባንክ ጋር የብድር አቅርቦት ስመምነት መደረሱ ለአርሶ አደሮች ትልቅ አቅም ይፈጥራል።