የእስቴ – ስማዳ መንገድ ግንባታ ዋና ዋና ሥራዎች ተጠናቀቁ።

17
ባሕር ዳር: ጥር 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በደቡብ ጎንደር ዞን የእስቴ – ስማዳ መንገድ ግንባታ ዋና ዋና ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ተከትሎ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ላይ መኾኑን ገልጿል።
የመንገዱ መገንባት ከዚህ በፊት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለመጓዝ የነበሩ እንግልቶችን የሚያስቀር ነው። ከዚህ አርሶ አደሮች የተለያዩ የአዝርዕት ምርቶቹን በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ የሚያስችል ነው።
በርካታ ከተሞችን ደረጃውን በጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት በማስተሳሰርም ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ መሥተጋብሩን የሚያጠናክር ነው።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ የተገነባ ሲኾን 50 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።
የ5 ድልድዮች እንዲሁም ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ከልቨርቶች ግንባታ ተከናውኗል።
የመንገድ ግንባታውን ዓለም አቀፉ የሥራ ተቋራጭ ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ አከናውኖታል። ሀገር በቀሉ ፕሮሚናንት ኢንጅነሪንግ ሶሉሽንስ ግንባታውን በመቆጣጠር እና በማማከር በኩል ተሳትፏል።
ፕሮጀክቱ ከፌደራል መንግሥት በጀት በተመደበ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ ነው የተከናወነው።
የአካባቢው አስቸጋሪ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የጸጥታ ስጋቶች እንዲሁ ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ በግንባታው ሂደት ላይ እክል ፈጥረው የነበረ ቢኾንም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመኾን ባደረገው የተቀናጀ ጥረት ፕሮጀክቱን ከግብ ማድረስ ተችሏል ነው ያለው አሥተዳደሩ።
ወገዳ ከተማ ላይ የሚቀሩ ጥቃቅን ሥራዎች በቀጣይ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሚጠናቀቁ ይኾናል ነው ያለው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሐሙሲት – እስቴ መንገድ ግንባታ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲኾን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleትልቅ ታሪክ፤ የላቀ ትስስር፤ የላቀ እቅድ፤
Next article“የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ይኾናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)