
ደብረ ብርሃን: ጥር 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ በጣይቱ ክፍለ ከተማ በሳሪያ ቀበሌ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
የሳሪያ ቀበሌ አርሶ አደር ተክልዬ አንተንይስሙ ከአሁን ቀደም በተሠራው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ልማት ሥራ አትክልት በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተከታታይ ዓመታት የተሠራው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ የአፈር ለምነትን በማሳደግ በኩል ለውጥ ማሳየቱን ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ መርሻ አይሳነው በከተማው በሚገኙ ቀበሌዎች ከዛሬ ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ለተከታታይ ለ30 ቀናት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
ከ15 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ የገለጹት ኀላፊው በ1 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ላይ ነባር 45 ተፋሰሶች የማጠናከር ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር ጸጋዎችን ለማበልጸግ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በመሥራት ሁሉም ተፈጥሮን ከጉስቁልና መታደግ አለበት ነው ያሉት።
የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሪ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ በመሥራት ተፈጥሮን በመንከባከብ የተፈጥሮ ጸጋዎችን መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በጋራ የሚለማው ልማት በግል ተጠቃሚ ያደርገናል ያሉት ምክትል ከንቲባው አሁን በተጀመረበት ርብርብ እና ግለት ማስቀጠል ተገቢ መኾኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አበበች የኋላሸት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
