
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የገታራ በራራ በሽሎ ወንዝ አሞር ገደል መሻገሪያ 91 ሜትር ተንጠልጣይ ድልድይ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
ድልድዩ በክልሉ መንግሥት እና ዓለም ባንክ መቀናጆ በጀት በገጠር ትስስር ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም ነው የተሠራው።
ድልድዩ በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ የገታራ በራራ በሽሎ ወንዝ በአስፈሪው አሞር ገደል መሻገሪያ የተሠራ ነው። 91 ሜትር የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድይ በፍጥነት እና በጥራት ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መኾኑን የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ቢሮ አስታውቋል።
ፕሮጀክቱ በወጣት ምሩቃን ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ደንቅ የገጠር መንገድ ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ ተቋራጭ የተገነባ ነው ተብሏል። ሄምሰ ኢንጂነሪንግ የድዛይንና ማማከር አገልግሎት መሥራቱም ተመላክቷል።
በድልድዩ አራት ቀበሌዎች እንደሚገኙ ተገልጿል። የክልሉ መንግሥት የአካባቢው ማኅበረሰብ የዘመናት ጥያቄን በመፈታቱ ምስጋና አቅርቧል። ድልድዩ አካባቢው ያለውን ጸጋ አውጥቶ ለመጠቀም እንደሚያስችልም ተመላክቷል።
ከአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ለድልድዩ በስኬት መጠናቀቅ የዞን እና ወረዳ አሥተዳደር መሪዎች እና ማኅበረሰቡ ድጋፍና ትብብር የሚደነቅ ነው ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
