
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ “የጥርን በባሕር ዳር” መርሐ ግብር አንዱ አካል የኾነው የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል።
በዘመቻው እየተሳተፉ ያገኘናቸው ወይዘሮ መልካም አልማው እንደገለጹት ከተማ ውብ የሚኾነው ማኅበረሰቡ ሲተባበር ነው። ማኅበረሰቡ ተጠቅሞ የሚጥለውን ቆሻሻ በአግባቡ እየለየ በቅርጫት መሠብሠብ እና ለጽዳት ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንዳለበት ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የጽዳት እና ውበት ሠራተኛ ብርሃን ጌታሁን በተሠማሩበት የከተማ ውበት ሥራ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። በአብዛኛው ማኅበረሰቡ ለጽዳት ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መኾኑን ነው የገለጹት።
ማኀበረሰቡ ቆሻሻን በሥነ ሥርዓት በአግባቡ በመሠብሠብ እና በተዘጋጀው ስፍራ ብቻ በማስቀመጥ ለጽዳቱ ባለቤት ኾኖ እንዲተባበር ጠይቀዋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር አካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጽጌረዳ አበበ ከተማዋ ጽዱ እንድትኾን በተደራጀ መንገድ የጽዳት እና ውበት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። የጽዳት ዘመቻው ከበዓል ማግሥት በየአካባቢው የሚጣለውን ቆሻሻ ለማስወገድ ታሳቢ ያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በርካታ ሁነቶች የሚከበሩ መኾናቸውን ያነሱት ኀላፊዋ ይህንን መሠረት በማድረግ ቀጣይነት ያለው የጽዳት የንቅናቄ ሥራዎች እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል። ከተማዋን ውብ እና ጽዱ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገው የጽዳት ዘመቻ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እየተከናወኑ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
ባሕር ዳር ከተማ ጽዱ እንድትኾን ለማድረግ ማኅበረሰቡ የኔ ኀላፊነት ነው ብሎ በማሰብ በየቦታው ቆሻሻን ባለመጣል ሊተባበር እንደሚገባ አንስተዋል። በግለሰብ ደረጃ ከቤቱ እስከ 20 ሜትር እንዲኹም ተቋማት ደግሞ እስከ 50 ሜትር ድረስ ማጽዳት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
