
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) ዩኒቨርሲቲዎች ጉና ተራራን በማልማት ጣና ሐይቅን ከእምቦጭና በደለል ከመሞላት ለመከላከል የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎቹ ሥምምነቱን የፈረሙት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን ጥሪ በመቀበል መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2012 ዓ.ም ሁለተኛውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በሃዋሳ ሲያስጀምሩ የደን ልማትን ለማስፋፋት ሁሉም ዜጎች በአንድ ልብ ሊተባበሩ ይገባል እንደሚገባ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ከጉና ተራራ የሚነሱ ወንዞችና መጋቢ ጅረቶች ተከዜንና ጣናን የሚሞሉ እንደመሆኑ ጉና ተራራን በደን መሙላት የተፈጥሮ ሃብቶችን ለመጠበቅ ዋስትና መሆኑን በማስገንዘብም ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎም ደብረታቦር፣ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ እንጂባራ እና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች የጉና ተራራ አከባቢን ለማልማት፣ በአካባቢ እንክብካቤና ሌሎች ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት ዛሬ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
“ጣናን ለመታደግ የጋራ፣ የትብብርና የፍቅር አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ወደ ጉና” በሚል መሪ መልዕክትም የጉና-ጣና ተፋሰስ ቦታዎች ላይ ችግኝ ተክለዋል፡፡
የጉና ተራራ የ41 ወንዞችና የ77 ምንጮች መገኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የጣናና የዓባይ ገባሮች በሙሉ የሚነሱበት እና የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ ተብሎ የሚጠቀስ ስፍራም ነው።
የጉና ተራራን ማልማት ጣና ሃይቅን ከእንቦጭ ለመጠበቅ እና ከደለል ለመከላከል እንደሚያስችል ምክረ ሀሳቦች በተደጋጋሚ እየቀረቡ ነው፡፡ ተራራውን ማልማት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስተማማኝ የውሃ አቅርቦት ለማግኘት እንደሚረዳም ይታመናል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡