
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ያቺ ጨለማ የወረሳት፣ የመከራ በትር የበዛባት፣ ዲያቢሎስ በጥርሱ የነከሳት፣ የሐጥያት ሕማም ያሰቃያት፣ ፍዳ ያስጨነቃት ዓለም መድኃኒቷን አገኘች፤ በብርሃን ተሞላች፤ በደስታም ከነፈች።
እነዚያ የእርሱን መምጣት በተስፋ የጠበቁት፣ የእርሱን መወለድ የጓጉለት፤ ለመዳን የተቻኮሉት፤ በናፍቆቱ የተጎዱት የበደል እስረኞች፣ የጥፋት ግዞተኞች፣ የዲያቢሎስ ምርኮኞች ከሐጥያት እስር የሚፈታቸው፣ ከመርገም የሚያወጣቸው፣ የሰው እጅ ያልሠራውን የብርሃን ልብስ የሚያለብሳቸው፤ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመልሳቸው እርሱ ኃያሉ አምላክ ተወለደላቸው።
ዓለምን እንደ ፈጠራት፣ እርሱ ይጠብቃታል፤ ከመራ ይከልላታል፤ እርሱም ያሳልፋታል። ከእርሱ ውጭ ዓለምን ማዳን የሚቻለው አልነበረም፣ የለም። አይኖርምም። እርሱ ነውና ዕውነተኛ መድኃኒት።
ንጽሒት ድንግል እመቤት የዓለሙን መድኃኒት ወለደችው፤ እናት ናት ሲሏት ድንግል፤ ድንግል ናት ሲሏት እናት የኾነች፣ እናትነቷ ድንግልናዋን ያልሻረባት፤ ድንግልናዋ እናትነቷን ያላስቀረባት፣ አስቀድሞ ገና በአምላክ ልብ የታሰበች፤ በንጽሕና የተጠበቀች፤ ሰማይና ምድር የማይችሉትን የቻለች፤ የሚታየው እና የማይታየው ዓለም የማይወስኑትን የወሰነች እመቤት ለዓለሙ ዕውነተኛውን መድኃኒት ወለደች። ዕውነተኛው መድኃኒት ተወልዷልና ዓለምም በብርሃን ተሞላች፤ በደስታ ከፍ ከፍ አለች።
ዕውነተኛውን ብርሃን፣ ዕውነተኛውን መድኃኒት፣ የዘለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን ወልዳለችና እመ አምላክ፤ እመ ብርሃን እየተባለች ተመሠገነች። እስከዘለዓለሙም እመ አምላክ ትባለለች። በዚህም ስም ከእርሷ ውጭ የምትጠራ ሴት የለችም። እርሱ ብርሃን እርሷ ደግሞ የብርሃን እናት ናትና።
አበው ከሚታየው እና ከማይታየው ዓለም አስቀድሞ በባሕሪው የነበረ፣ ፍጥረታትን እጹብ ድንቅ አድርጎ የፈጠራቸው አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰው ኾኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ይልቃል ይላሉ። ስለ ምን ቢሉ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፤ በዮርዳኖስ ተጠምቆ፣ በቀራንዮ ተሰቅሎ የማይሞተው ሞቶ፣ ሞትን በኀይሉ እና በሥልጣኑ ድል ነስቶ የሰውን ልጅ ከመከራ አድኖታል፤ ከግዞት አውጥቶታልና።
በርእሰ አድባራት ወ ገዳማት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የአራቱ ጉባዔያት መምህር ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ “የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ታላቁ ደስታችን ነው፤ ከእርሱ ደስታ ውጭ ያሉት ደስታዎች ሁሉ የሚተኩ ናቸው፤ የእርሱ ደስታ ግን አይተካም” ይላሉ።
ልብስ በልብስ ይተካል፤ እቃ በእቃ ይተካል፤ ጓደኝነት በብቸኝነት ይተካል፤ ጤና በሕመም ይተካል፤ ሕይወት በሞት ይተካል፤ ማግኘት በማጣት ይተካል፤ ሹመት በሽረት ይተካል፤ መልበስ በመራቆት ይተካል፤ መልከኛነት በመጠውለግ ይተካል፤ ጉልበት በእርጅና ይተካል፤ እርስት በስደት ይተካል፤ ዝና በመረሳት ይተካል፤ ሁሉም ያልፍና ደስታችን ይረግፋል። የማይወሰድ፣ የማይነጠቅ፣ የማያልቅ፣ የማያልፍ ፍጹም ደስታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ይላሉ።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለነፍስም ለስጋም ታላቁ ደስታችን ነው፤ እርሱ ተወልዶልናልና ታላቁ ደስታችን ነው፤ መንግሥቱ ፍጹም የኾነ ንጉሥ ክርስቶስ ተወልዷልና ታላቁ ደስታችን ነው፤ መድኃኒታችን ተወልዷልና ደስታችን ነው። ለዓለም ሁሉ የሚበቃ ደስታ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ማንም የለም ነው የሚሉት።
ልብስ በልብስነቱ ደስ ቢያሰኝ ጤናን አይሰጥም፤ ምግብ ልብስ አይኾንም፤ መልክ ኀይል አይኾንም፤ አንዱ አንዱን ይኾናል እንጂ ለሁሉም አይኾንም ክርስቶስ ግን ለሁሉም ይኾናል፤ እርሱ ልብስም ምግብም፣ መድኃኒትም ነውና ይላሉ።
የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታል እንደተባለ በጥምቀት እንለብሰዋለን፤ የሕይወት እንጀራችን ነው፤ የሕይወት መጠጣችን ነው፤ መድኃኒታችን ነው፤ ክርስቶስ ንጉሳችን ነው ይፈርድልናል፤ ክርስቶስ አባታችን ነው የማታልፍ መንግሥቱን ያወርሰናል፤ ትንሳኤ እና ሕይወት ነው ይላሉ።
እርሱን የታመነ ቸር እረኛ ነው፤ ራሱን ለበጎቹ አሳልፎ የሚሰጥ፤ የመነኮሳት ተስፋቸው፤ የካህናት ሿሚያቸው አክባሪያቸው፤ የሰማዕታት አክሊላቸው ነውና ልደቱ ታላቁ ደስታ ነው። ክርስቶስ ከአስጨናቂ እጅ ፈልቅቆ ያወጣ፤ የሞትን ጥርስ አውልቆ የሰው ልጆች በሞት ላይ እንዲረማመዱ ያበረታ ነው።
ክርስቶስ ከመንበረ መንግሥቱ ሳለ ወደዚህ ዓለም መጣ፤ በዚህም ዓለምም በማይመረመር ምስጢር የእናቱን ድንግልና ሳይለውጥ ተወለደ። አንበሳን በግ ታቀፈው፣ እሳትን ሰው በጉያው ያዘው፣ መብረቅን የሰው ልጅ አዘለው ቢባል የሚያምን የለም፤ በድንግል ማርያም ማሕጸን ግን የክብር መብረቅ ተወሰነ፤ በረዶ እና እሳት በአንድ ላይ ተስማምተው አደሩ ነው የሚሉት ሊቁ።
ሐጥያትን የሚያስተሰርይ ዕውነተኛው ብርሃን ተወልዷልና ዛሬ ፍጹም ተድላ ደስታ ነው፤ ነጻነታችንን ሊመልስልን፤ ያጣናውን ልጅነት ሊሰጠን፤ ከሠለጠነብን ደዌ ሊያወጣን እርሱ መጥቷልና ደስታ ነው ይላሉ።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ከሰማይ እስከ ምድር ድረስ መጥቷል፤ የሰው ልጅ ውድቀት አምላክን ከሰማይ እስከ ምድር ያመጣ ነበር ነው የሚሉት።
ክርስቶስ ዕውነተኛ እረኛ ስለኾነ በከብቶች በረት ተወለደ፤ ዕውነተኛ መስዋታችሁ እኔ ነኝ ሲል በበረት ተወለደ፤ ብርሃናችሁ እኔ ነኝ ሲል በጨለማ ተወለደ፤ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝም ጨለማን ከቶ አያይም፤ የሕይወትን ብርሃን አግኝቶ ይኖራል እንጂ እንዳለ። የሕይወት እንጀራ ነኝ ሲል በቤተልሔም ተወለደ ይላሉ።
ብርሃናችን ክርስቶስ ተወልዶልናል እንደሰታለን ነው የሚሉት። በእርሱ ከተደሰትን ደስታችንን የሚቀማን የለም ይላሉ። ከመከራ ሊዋጀን ወደዚህ ዓለም መጥቷል፤ እርቃናችንን ሊያለብስ እርቃኑን ተወለደ፤ ሰላምን ሊሰጠን ከመላዕክት ጋር ሊጨምረን እርሱ ተወለደልን ይላሉ።
እነኾ ታላቁ ደስታ የኾነባት፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት፣ ሰው እና መልአክት በአንድነት የዘመሩባት፤ ምድር በዕውነተኛው ብርሃን የተመላችባት፤ ዕውነተኛው መድኃኒት ወደ ምድር የመጣባት፤ የሰው ልጅ ከዓመተ ፍዳ ወደ ዓመተ ምህረት የተሸጋገረባት ቀን ዛሬ ናትና ደስ ይበላችሁ።
እነኾ ዓለም መድኃኒቷን አግኝታለች፤ በደስታም ተሞልታለች።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
