
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው ፋና ሕጻናት እና የማኀበረሰብ ልማት ማኀበር የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ለ149 አረጋውያን የማዕድ ማጋራት እና የቅርጫ ሥጋ ሥጦታ አበርክቷል።
የማዕድ እና የቅርጫ ሥጋ ሥጦታ ተጠቃሚ የኾኑት እማሆይ ዓለም ፈንታ የሚጦራቸው እና የሚደግፋቸው ልጅ ስለሌላቸው በዓሉን እንዴት አሳልፍ ይኾን እያሉ ይጨነቁ እንደነበር ተናግረዋል።
“ማኅበሩ መልካም ምሳ መግቦ እና የቅርጫ ሥጋ ድጋፍ ስላደረገልኝ ቤቴ እንደሞላ ተሰምቶኛል። ዛሬ ብቻ ሳይኾን ነገየንም ብሩህ አድርጎልኛል” ነው ያሉት።
የወለዱት ልጅ ባይኖርም ሰጭው ሕዝብ ሁሉ የእሳቸው ልጅ መኾኑን ዛሬ መረዳታቸውን አውስተዋል።
“ሀገሬን እና ሕዝቤን ክፉ አይንካብኝ”ሲሉም መርቀዋል።
ሌላዋ እናት ላዋይ ታደሰ ሀገር እና ሕዝብ ሰላም ሲኾንማ ጧሪም በመኖሩ ዛሬ ተደስቼ ውያለሁ ነው ያሉት።
እቴናት መኮንን በበኩላቸው ቅን የኾነው ሕዝብ ቤት ሠርቶ፣ ቀለብ ሰፍሮ እና በየዕለቱ እየጠየቀ ሕይዎትን በደስታ እንዲኖሩ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
ዛሬም የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ስለተደረገላቸው የምሳ ግብዣ እና የቅርጫ ሥጋ ድጋፍ አመሥግነዋል።
የፋና ሕጻናት እና ማኀበረሰብ ልማት ማኀበር ሥራ አሥኪያጅ ዳኛቸው ደርሶ ማኀበሩ ላለፉት 18 ዓመታት አረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
በዘመን መለዋጫ፣ በትንሳኤ እና በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በቋሚነት ለአረጋውያን እና ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
የዘንድሮውን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ 149 ጧሪ እና ደጋፊ ለሌላቸው ወገኖች ከ550ሺህ ብር በላይ ወጭ በማድረግ የቅርጫ ሥጋ ሥጦታ እና ምሳ የማብላት ሥነ ሥርዓት መደረጉን ተናግረዋል።
ትናንትም አቅመ ደካማ ለኾኑ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ቤት ለቤት በመዘዋወር የዶሮ ሥጦታ ማድረጋቸውን ሥራ አሥኪያጁ አስታውሰዋል።
የሥነ ሥርዓቱ የክብር እንግዳ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አያሌው አባተ (ዶ.ር) ዛሬ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የደስታ ዕለት ነው ብለዋል።
በደስታ የሚከበረው ደግሞ ለመንፈስ እርካታን በሚሰጥ፣ ዕኩልነትን ባከበረ፣ አረጋውያን እና አቅመ ደካሞችን በደገፈ መንገድ እንደኾነ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በዓሉም የተጠቀሰውን እንደሚያሟላ አስረድተዋል።
ፋና ሕጻናት እና የማኀበረሰብ ልማት ማኀበር ጧሪ የሌላቸውን እናቶች፣ አባቶች እና ሕጻናት ሠብሥቦ ያደረገው የበጎ ምግባር የሚወደስ እና እኛም በቋሚነት አጋዥ እንድንኾን የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
