
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጉምሩክ ኮሚሽን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መሪዎች እና ሠራተኞች የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ በዝግባ የሕጻናት እና አረጋውያን መረዳጃ በጎ አድራጎት ድርጅት ማዕድ አጋርተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ዝግባ የሕጻናት እና አረጋውያን መርጃ ድርጅት ስለሚያደርገው የበጎ አድራጎት ሥራ አመሥግነዋል።
የከተማ አሥተዳደሩም በቀጣይ እገዛ እንደሚያደርግለት ገልጸዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሠራተኞች ላደረጉት ድጋፍ አመሥግነዋል። ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም የበጎ አድራጎት ሥራውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በጉምሩክ ኮሚሽን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጅ አለነ መሀሪ ኮሚሽኑ ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ ችግረኛ ወገኖችን ለመርዳት በሠራተኞች ተነሳሽነት ወስነው ማዕድ ማጋራታቸውን ገልጸዋል።
የዝግባ ሕጻናት እና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አሥኪያጅ ስለሺ ጌታቸው ድርጅታቸው ላለበት አካባቢ አገልግሎት ለመስጠት መቋቋሙን አስታውሰው ዛሬ ላይ ሰፍቶ የከተማውን ሕዝብ እያገለገለ መኾኑን ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ ከውጭ ጥገኝነት በመላቀቅ ችግረኞችን የመደገፍ ሥራውን ለማሳደግ ከበጎ አድራጊዎች ጋር በመተባበር እና የገቢ ማስገኛ በመሥራት እያገለገለ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ሥራ አሥኪያጁ ድርጅታቸው አረጋውያንን በመንከባከብ እና ሕጻናትን በማስተማር ጭምር እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን በልደት በዓል ለአረጋውያን እና ሕጻናት ላደረገው የማዕድ ማጋራት እና በሥራው የተሳተፉትንም አመሥግነዋል።
በማዕድ ማጋራቱ ተካፋይ አዛውንቶች ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት በዓልን አስመልክተው ማዕድ ያጋሯቸውን አመሥግነዋል።
አቅመ ደካሞችን መደገፍ ከፈጣሪ ስንቅ ነው ያሉት አረጋውያኑ አስታዋሽ ስላላቸውም ደስተኛ እንደኾኑ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
