
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር በመኾን፣ የክረምት በጎ አድራጎት መርሐ ግብርን ወደ ላቀ ከፍታ ያሸጋገረውን የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን በይፋ መርቀናል ብለዋል።
ይህ ሞዴል መንደር በ7 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው። እያንዳንዱ ቤት ሁለት መኝታ ክፍሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ክፍሎች እንዲኖሩት ተደርጎ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ ነው።
መንደሩ በቤተሰብ ደረጃ ለ150 ዜጎች ምቹና ጽዱ መኖሪያ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑን ገልጸዋል። የመሠረተ ልማት አቅርቦቱም የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የኤሌክትሪክና የሶላር ኃይል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስፍራ እና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ያካተተ ነው።
የነዋሪዎቹን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት ለማሻሻል መንደሩ የምርትና የገበያ ሰንሰለትን ያካተተ የተቀናጀ አሠራርን ዘርግቷል። ይህ የልማት ሥራ የወተት ላሞች፣ የዶሮ እርባታን እና የጓሮ አትክልት ልማትን አጣምሮ የያዘ ነው። እስከ መገበያያ ስፍራ የሚደርስ የተቀናጀ የንግድ ሰንሰለት ተፈጥሮለታል ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
