
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትርጉም ያለው መንፈሳዊ በዓል ነው።
የልደት በዓል የአምላክን ሰው መኾን እና ለዓለም መድኃኒት ኾኖ መወለዱን የሚገልጽ ታላቅ በዓል ነው።
የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀበትን ታላቅ የምሥራች የሚያበስር በዓልም ነው።
በዓሉ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ወይም የገና በዓል እየተባለ ይጠራል። ገና እና የልደት በዓል የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት የሚያታሰብባቸው ናቸው። በስያሜ፣ በትውፊት እና በአከባበር በኩል የተወሰኑ ልዩነቶች ይታዩባቸዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ትኩረቱ መንፈሳዊው ላይ ሲኾን ገና ሲባል ግን የክርስቶስ ልደትን መንፈሳዊ በዓል ተከትለው የሚመጡ ማኅበራዊ ትውፊቶችን፣ ሥነ ሥርዓቶችን እና የደስታ መግለጫን የሚያመለክት ነው።
በማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኒዓለም ቤተ ክርስትያን የአራቱ ጉባኤያት ምክትል መምህር መምህር ዘላለም ሀዲስ ገና የሚባለው ኢየሱስ ክርስቶስ በከብቶች በረት ሲወለድ የክርስቶስን መወለድ ተከትሎ በበረቱ ውስጥ የነበሩት እረኞች የተጫወቱት የደስታ መግለጫ ነው ብለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በከብቶች በረት ሌሊት ሲወለድ ቤተልሔም በብርሃን ደምቆ ለእረኞችም ብርሃን ኾኖላቸው። ገና የሚባለውን ጨዋታ እየተጫወቱ ደስታቸውን ገልጸዋል ይላሉ።
መላዕክትም ከእረኞች ጋር ተቀላቅለው የተጫወቱበት በዓል በመኾኑ “በዓለ ገና” እየተባለ ይጠራል ነው ያሉት። ይህንን መነሻ በማድረግም የልደት በዓል የገና በዓል እየተባለ እንደሚጠራ አስረድተዋል።
በተአምረ ማርያም መቅድም ላይም በዓለ ገና ተብሎ መጠቀሱን እና የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል የሚገልጽ እና የሚያደምቅ በዓል መኾኑን ነው ያስረዱት።
እንደ መምህር ዘላለም ማብራሪያ የገና በዓል የሚለው የክርስቶስ ልደትን በዓል የሚገልጽ እና ልደቱን የሚያጎላ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ለገና በዓል ወይም ለገና ጨዋታ ምክንያት ነው ያሉት መምህር ዘላለም ነገር ግን የገና በዓል ራሱን የቻለ ሌላ በዓል አለመኾኑን ይገልጻሉ።
የገና በዓል እረኞች የክርስቶስን መወለድ አስመልክተው ደስታቸውን የገለጹበት ባሕላዊ ጨዋታ ከመኾኑ ባለፈ ሌላ ራሱን የቻለ ሃይማኖታዊ ትውፊት እንደሌለውም ገልጸዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
