
ባሕር ዳር: ታሕሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ እየተከበረ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤሊያስ አብርሃ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲሁ ልደት አልነበረም፤ ድንቅ እና ረቂቅ ነው እንጂ ብለዋል፡፡
በልደቱ ሰውና መላእክት የዘመሩበት፣ ዝቅተኛ ይባሉ የነበሩት እረኞችም በልደቱ አመስጋኞች፣ አክባሪዎች የኾኑበት፣ ፍቅር እና ትህትና የተገለጠበት ታላቅ በዓል መኾኑን ተናግረዋል።
እነኾ ወደ ቤተልሔም እንሂድ፣ እግዚአብሔር የገለጠልንን እንይ እያሉ ወደ ቤተልሔም መሄዳቸውን ተናግረዋል። የተወለደው እግዚአብሔር ነው፤ የተወለደው የዓለም መድኃኒት ነው ብለዋል። በልደቱ በረከትን እንደሰጠም ገልጸዋል።
የልደት በዓል የድኅነት በዓል ነው ያሉት ንቡረ እድ ኤሊያስ አብርሃ ክርስቶስ የተወለደው ሰውን ለማዳን ነው ብለዋል፡፡ ሰው በበደሉ ምክንያት በጨለማ ውስጥ ይኖር ነበር፤ ክርስቶስም ተወልዶ አዳነው ነው ያሉት፡፡ የክርስቶስ ልደት ዓለምን ከመርገም ያዳነ መኾኑንም ተናግረዋል፡
የክርስቶስ ልደት የምንድንበት ቤዛችን ነው፣ ፍጥረት ሁሉ የሚድነው፣ ሰላም የሚያገኘው እና የሚከብረው በክርስቶስ ቤዛነት ነው ብለዋል፡፡ ያለ እርሱ ዓለም አትድንም ነው ያሉት፡፡
በላሊበላ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እና የቅዱስ ላሊበላ ልደት በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት ሲከበር መኩራት እና መደሰት አለብን፤ እግዚአብሔር መርጦናል፣ ባርኮናልና ነው ያሉት፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን የራሱ ማዳሪያ እና የስሙ መጠሪያ አድርጎ መርጧታል ነው ያሉት። እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የሰጠው ፀጋ ታላቅ ነው፤ ይህን ታላቅነት አክብረን እንያዝ ብለዋል፡፡ ታላላቆቹ እነ ቅዱስ ላሊበላ ተቀድሰው፤ ሀገራችንን ቀድሰው ታላቅ አድርገውልን አልፈዋል፤ እነሱን ልንመስላቸውና ልንከተላቸው ይገባል ብለዋል።
በዓሉ ሀገራችንን ኢትዮጵያ የተባረከችበት፤ ሕዝብም የተባረከበት እና የተቀደሰበት መኾኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
