
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ከምታከብራቸው ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አንዱ ነው።
“ክብር ለእግዚአብሔር በሰማይ፤ ሰላምም በምድር ” የሚለው መልዕክት የልደቱ ዋና ትርጓሜ መኾኑን የተናገሩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የምሥራቀ ፀሐይ ይድበራ ማርያም የመጻሕፍት መምህር እና የስብከተ ወንጌል መምህሩ ይኸይስ የሻንበል ናቸው፡፡
ክርስቶስ ሰው ኾኖ መወለዱ የእግዚአብሔርን ፍቅር በተግባር ያሳየበት ታላቅ ምስጢር እንደኾነ ተናግረዋል። ልደት ሰውን ከጥላቻ እና ከበቀል ወደ ይቅርታ ያመጣ፣ በሰዎች መካከል ያለውን ጥላቻ በፍቅር እንዲፈታ መንገድ የከፈተ መኾኑንም አስርድተዋል፡፡
ልደቱ የጦርነት መቋረጥ ብቻ ሳይኾን የልብ እርቅን የሚያበረክት መንፈሳዊ መልዕክትም ነው ብለዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በበረት ውስጥ መወለዱ ሰው ሁሉ እኩል መኾኑን ያሳዬ፣ ተስፋ እና ምኞት የተፈጸመበት ታላቅ ክስተት መኾኑንም መምህሩ ገልጸዋል፡፡
የክርስቶስ ልደት የጠፋችውን ዓለም ከድካም ያነሳበት፣ ደክማ የነበረችውን ያበረታበት፣ ወድቃ የነበረችውን ያነሳበት፣ የተጨነቀው የተረጋጋበት እንደኾነም ተናግረዋል። ለአዳም እና ለሔዋን ልዩ የደስታ ቀን በመኾን ለዓለም ሰላም ታላቅ አስተዋጽኦ በተግባር የተተረጎመበት ነውም ብለዋል መምህሩ፡፡
መምህር ይኸይስ በዓሉ ሲከበር በምግብ እና በመዝናናት ብቻ ሳይወሰን የመንፈሳዊ ተግባራት በመከወን ጭምር መኾን አለበት ነው ያሉት።
በልደት ወቅት ይቅርታ ማድረግ እና መጠየቅ፣ ከጎረቤት እና ከማኅበረሰቡ ጋር ማዕድ መጋራት እና ፍቅርን ማሳየት፣ ልዩነትን ሳይኾን አብሮነትን ማስቀደም፣ የጥላቻ ቃልን በየቀኑ ከልባችን ማስወገድ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ክርስቶስን ለሺህ ዘመናት የሰበከች ሀገር ናት” ያሉት መምህር ይኸይስ የክርስቶስ ልደት ደግሞ ከስብከቶቿ ዋነኛው ክፍል እንደኾነ አንስተዋል፡፡ እንደ አስተምህሮውም ልደት ክርስቶስን ከልባችን መውደድ ማለት ነው፤ ክርስቶስን ከልብ የወደደ ጦር አያነሳም ዛሬ የሚታዩት ግጭቶች፣ ጥላቻ እና መከፋፈል ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ ጋር ፈጽሞ የማይሄዱ ናቸው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የኦርቶዶክስ እምነት አስተምህሮ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ይላል፣ ግድያን እና ጥላቻን ይከለክላል፣ ሰላምን እንደ መንፈሳዊ ግዴታ ያስተምራል ነው ያሉት፡፡
የክርስቶስ ልደትም የዓለም ሰላም መልዕክት ሲኾን፣ ዛሬ ለኢትዮጵያ ከምንም ጊዜውም በላይ የሚያስፈልጋት መንፈሳዊ መፍትሔ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ልደትን በፍቅር፣ በይቅርታ እና በአብሮነት ስናከበር ብቻ ነው ክርስቶስ የሰጠንን የዓለም ሰላም መልዕክት በሀገራችን መገንባት የምንችለው ብለዋል፡፡
ስለዚህ ሰላምን ለማምጣት ከልብ ይቅርታን ዛሬውኑ መጀመር ይገባናል፤ ንስሐ፣ ይቅርታ እና መግባባት የሰላም መሠረቶች ናቸው ነው ያሉት። መንፈሳዊ መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች በአንድነት ሰላምን ማስተማርእንዳለባቸውም መምህሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡ -ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
