
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ እየተከበረ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የልደት በዓል በላሊበላ በጉጉት የምናከብረው በዓል ነው ብለዋል፡፡
ይህን ድንቅ እና ታላቅ በዓል ስናከብር ጎጂ ነገሮችን የምንለይበት፣ መልካሙን የምንመርጥበት፣ የትናንት ድንቅ ታሪካችንን የምንዘክርበት፣ ዛሬ ላይ እጋጠሙ ያሉ የድህነት እና የግጭት አዙሪቶችን ታግለን በማሸነፍ የነገ ተስፋችንን የምናድስበት መኾን አለበት ነው ያሉት።
በክልሉ በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አጋጥሟል ብለዋል። በግጭቱ ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት።
መነግሥት ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ሰላም የሁሉም ሰው የጋራ ሃብት እንደመኾኑ መጠን የጋራ ትብብርን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የታጠቁ ኃይሎችን በመምከር ለውውይት ዝግጁ እንዲኾኑ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ለሰላም ከመንግሥት ጎን ኾነው እንዲሠሩም አስገንዝበዋል፡፡
በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር በማድረግ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ልማት ወደ ነበረበት መመለስ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ቅርሱን በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላፍ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል። በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
