“ለነድያን የሚሰጥ ስጦታ ለእግዚአብሔር እንደተሰጠ ይቆጠራል” ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላዕክ

9

 

ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 26/2018ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከሌሎች በዓላት በተሻለ ሰዎች ስጦታዎችን የሚለዋወጡበት በዓል ነው። ስጦታ የመለዋወጥ ተግባሩ ሃይማኖታዊ መሠረት መኖር እና አለመኖሩን ብዙዎች አይገነዘቡትም።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባኤያት መምህር እና የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላዕክ እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለጠልን አንድ ልጁን ሳይሳሳ በመስጠት ነው ብለዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን የስጦታ ቀን የምንልበት አንዱ ምክንያትም ይህ እንደኾነ ነው የገለጹት። በቅዱስ ወንጌል ላይ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ላይም አንድ ልጁን እስከ መስጠት እንዲሁ ዓለሙን ወደደው በሚል የተነገረው ኢየሱስ ክርስቶስ በስጦታ መሠጠቱን ያስገነዝባል ብለዋል።

ጌታ በተወለደበት ዘመን እና ቦታ የነበሩ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን አግኝተው ለክርስቶስ ያላቸውን ስጦታ እንደየ አቅማቸው መስጠታቸውን ጠቅሰዋል። የማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ላይ እንደተገለጸውም ነገሥታት ወርቅ ስላላቸው የወርቅ ሳጥናቸውን ይዘው ሂደው ሳጥኑን ከፍተው ወርቅ ሰጥተውታል፤ እረኞች ምንም ስላልነበራቸው ምስጋና አቅርበውለታል ነው ያሉት።

እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ከታናናሻችሁ ለአንዱ ማድረጋችሁ ለእኔ ማድረጋችሁ ነው ብሎ ስለተናገረ ለእሱ መሥጠት ከፈለግን ዛሬ ላይ ለነድያን ስጦታ እንስጥ ነው ያሉት። “ለነድያን የሚሰጥ ስጦታ ለእግዚአብሔር እንደተሰጠ ይቆጠራል” ብለዋል። በዓሉ ከስጦታ ጋር የሚገናኝበት ሌላኛው ምክንያት ይሄ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ልዩ ቀን ትልቁ የፍቅር ስጦታ የተገለጠበት ቀን ነው ያሉት ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላዕክ በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ስጦታ መስጠት የጀመሩት ሰብዓ ሰገል ናቸው፤ በዚህ ቀን ከተደረጉ ነገሮች መካከል አንዱ የኾነውን የስጦታ መለዋወጥ ለማስታወስም ስጦታ እንለዋወጣለን ብለዋል ።

በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን ዘመድ ብቻ ተፈልጎ ስጦታ አይሰጥም፤ ለማንኛውም ፍጥረት ነው የሚሰጥ ሰብዓ ሰገልም ክርስቶስን አይዘመዱትም ነበር ነው ያሉት። አላውቀው ብለውም የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው እያሉ ፈልገው መጠው ነው ስጦታ የሰጡት ነው ያሉት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋማትም ኾነ ማኅበረሰቡ ያለው የበዓል ስጦታ የመስጠት ተሳትፎ እና ንቃትም የሚበረታታ መኾኑን አንስተዋል። ሰብዓዊነትን ማስቀደም ግን አሁንም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።

ለበዓሉ የሚስማማ ሰብዕና መገንባት መልካም እንደኾነም ተናግረዋል። ቤተልሔም ላይ የተወለደው ክርስቶስ እኛን ፍለጋ ነው የመጣው፤ እኛም ምንም ሳንፈልግ ሰዎችን እንፈልግ፣ ማገዝ እናስቀድም በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ.ር) መልዕክት፦
Next article“የልደት በዓል በላሊበላ በጉጉት የምናከብረው በዓል ነው” አቶ አራጌ ይመር