ድጋፉ ባይደረግልን ኖሮ ጾም ሳንፈታ እንውል ነበር።

15
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 28/2018 (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ፣ ከግሬስ ለልጆች እና ቤተሰቦቻቸው ማዕከል እና ከዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ የበዓል መዋያ ድጋፍ አድርጓል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለበዓሉ የማዕድ ማጋራት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመተባበር ድጋፉን ያደረጉ አካላትንም አመሥግነዋል።
መደጋገፍ ባሕላችን ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው መንግሥታዊ ባህሪ እንዲኖረው ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ለማድረግ ቅን ልቦና ካላቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ገንዘቡ መሠብሠቡንገልጸዋል።
ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ”የሰውን ልጅ ችግር የማይፈታ ሃብት ምንም አይጠቅምም” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ካላቸው ቀንሰው የደገፉ ባለሃብቶችን እና የተቋም መሪዎችን አመስግነዋል። ሌሎችም አርዓያውን እንደሚከተሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ለመረዳዳት ሰው መኾን በቂ ነው፤ በዓልን ብቻ ሳንጠብቅ መረዳዳትን አጠናክረን እንቀጥል፤ በዓሉን በየሰፈሩም በመረዳዳት እናሳልፍ ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል መዋያ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ዛሬ ለ420 ወገኖች 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የበዓል መዋያ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
ለእያንዳንዳቸውም 25 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ አምስት ሊትር ዘይት እና አንድ ዶሮ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ለበዓሉ ድጋፍ ለማድረግ ከተለያዩ ግለሰቦች እና ተቋማት 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር መሠብሠቡን ገልጸዋል። በዚህም ለ22 ሺህ 375 ወገኖች ድጋፍ እንደሚደረግ ነው ያስረዱት።
ለበዓላት ቀን ብቻ ሳይኾን በሌሎች ቀናትም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ድጋፉ የተደረገላቸው ወገኖችም የተደረገላቸው ድጋፍ በዓልን በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። በድህነት እንደሚኖሩ የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ ድጋፉ ባይደረግላቸው ኖሮ ጾም ሳይፈቱ ይውሉ እንደነበርም ገልጸዋል።
ያለው ለሌለው ማካፈል በሰማይም በምድርም ይጠቅማል፤ ሌሎቹም ለችግረኞች ድጋፍ እንዲያደርጉ እንጠይቃቸዋለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ: ዋሴ ባዬ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleቀልጣፋ እና ምርታማ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት ላይ ትኩረት ተደርጓል።
Next articleየገና ጨዋታ የእኩልነት መገለጫ ነው።