
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 28/2018 (አሚኮ) የአማራ ክልል የከተማ ዘርፍ ተቋማት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በዘርፉ የ25 ዓመታት ፍኖተ ካርታ እና የአምስት ዓመታት ስትራቴጅክ ዕቅድ መሠረት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የተቋማት አደረጃጀትን በማስተካከል ወደ ተግባር እንዲገቡ መደረጉንም አንስተዋል።
ተቋማትን በማሥተሳሰር ቀልጣፋ እና ምርታማ የኾነ የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ በፋይናንስ እና በጥሬ እቃ አቅርቦት ላይ የተሻሉ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
ባለፉት ወራት 41 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠብ መቻሉንም አንስተዋል። የከተሞች ገቢ እየተሻሻለ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
በቱሪዝም ልማት፣ በቅርስ ጥበቃ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም መልካም አፈጻጸሞች ታይተዋል ነው ያሉት። በኮሪደር ልማት እና በቤት ልማት መርሐ ግብርም በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ዘርፉ መነቃቃት የታየበት፣ የተሻለ ድጋፍ፣ ክትትል የተደረገበት እና አዳዲስ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ የመጡበት እንደነበር አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ታምርት፣ የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እና ኢንቨስትመንት መሳብ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
ለኢንዱስትሪዎች ማነቆ የኾኑ ችግሮችንም በመለየት ለመፍታት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
በተደረገው ክትትል እና ድጋፍም ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው 62 በመቶ ደርሷል ብለዋል። በዚህም ምርታማነት ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት። ከ1ሺህ 800 በላይ አዳዲስ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) ባለፋት ስድስት ወራት በምርት አቅርቦት፣ ሕገ ወጥነትን በመከላከል እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተሻሉ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል።
ለኢንዱስትሪዎች የሚኾን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ግብዓት ማቅረብ መቻሉንም ተናግረዋል። 13 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የኀብረተሰቡን ጤና የሚጎዳ ምርት እንዲወገድ ተደርጓል ነው ያሉት።
በተለያዩ ቦታዎች ኬላ በመጣል ያልተገባ ቀረጥ ያስከፍሉ የነበሩ አካላትንም ማስቆም ችለናል ብለዋል።
የነዳጅ አቅርቦት እንዲሻሻል ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል። 18 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ነዳጅ በቁጥጥር ስር በማዋል ለመንግሥት ገቢ መደረጉንም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
