
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 28/2018 (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ 381 ቤቶችን ከሙሉ የቤት ዕቃና ከበዓል ማሳለፊያ ጋር በስጦታ አስረክቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ 381 ቤቶችን ከሙሉ የቤት ዕቃና ከበዓል ማሳለፊያ ጋር በስጦታ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ቤቶች መካከል 273ቱ ቀደም ሲል የወዳደቁ የቀበሌ ቤቶች የነበሩ እና ሙሉ በሙሉ ፈርሰው እንደገና በመገንባት ለቀድሞ ለነዋሪዎች የተላለፉ ናቸው ብለዋል።
108 ደግሞ ለአቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች፤ ለሀገር የአካል ዋጋ ለከፈሉ የጀግናው የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት፤ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ለሀገር ባለውለታዎች አስተላልፈናል ነው ያሉት።
ቤቶቹ የሕፃናት መጫወቻን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች የተሟሉላቸው፣ አዲስ የተገነቡ ዘመናዊ መንደሮች ናቸው ብለዋል።
ከተማችንን ውብ አበባ ስናደርግ፣ የነዋሪዎቻችንን የኑሮ ዘይቤ በማዘመን እና የኑሮ ጫናዎችን እያቃለልን ጭምር ነው ።
በከተማዋ ከለውጡ ወዲህ በሰው ተኮር እሳቤ እየተመራን የበጎ ፍቃድ ተሳትፎ ባሕል እየኾነ በመምጣቱ 45 ሺህ ቤቶችን በበጎ ፍቃድ ተሳትፎ በመገንባት ለማኅበራዊ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች እና ለሀገር ባለውለታዎች በማድረስ እምባቸውን ማበስ ተችሏል ነው ያሉት።
“ሃምሳ ሎሚ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነው” እንደሚባለው ሁላችንም እየተባበርን ጊዜያዊ ችግሮችን በጋራ በመሻገር ለዘላቂ ልማት እንተጋለን ብለዋል።
ለበጎ ፍቃደኞችና ለአስተባባሪዎች በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
