የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር ለምን በኢትዮጵያ ተለየ?

18
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 28/2018 (አሚኮ) በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አንዱ ነው።
የዚህ በዓል አከባበር ሥርዓት ሃይማኖታዊ መሠረት ቢኾንም በሀገራት መካከል አከባበሩ ልዩነቶች ይስተዋልበታል። ልዩ ከኾነባቸው ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ናት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረስብከት የአራቱ ጉባኤያት መምህር እና የሊቃውንት ጉባኤ ሠብሣቢ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላክ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር ላይ በዓለም ሀገራት መካከል ልዩነት ከሚፈጥሩ ጉዳዮች አንዱ የሀገራት የየራሳቸው የቀን መቁጠሪያ ሥርዓት መኖር መኾኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ከበዓል ባሻገር የአከባበር ሥርዓቱን ወደ ባሕል ማስገባታችንም ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።
ሃይማኖት መጽደቂያ እና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግቢያ ነው፤ ባሕል ደግሞ ከኅብረተሰቡ ጋር ተሳትፎ ማድረጊያ የጋራ እሴት ነው፤ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሃይማኖቱ ባሻገር ባሕል ጭምር ማድረጋችን የበዓል አከባበሩን ከሌሎች ሀገራት እንዲለይ አድርጎታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያለው ሥነ ሥርዓት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበርን ልዩ አድርጎታል ነው ያሉት።
በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ያለው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ፣ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ ቅዳሴ፣ ማህሌት፣ የታቦት ንግሥ እና መንፈሳዊ ዝማሬ የምዕራባውያን በዓል አከባበር ላይ እንደሌለ ጠቅሰዋል።
በመንፈሳዊ አተያይ ላያስፈልጉ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ሕዝቡ የሚያሳያቸው እና የበዓሉ አካል ኾነው የቀጠሉ ኾታ እና እልልታ ሰርግ እና ሌሎች ኹነቶች ላይ ከሚዘፈነው ዘፈን የተለየ ግጥም ያለው ዜማ እስክስታ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ የዓለም ሀገራት ላይም የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል የማክበር አጋጣሚ እንደነበራቸው ያስታወሱት ሊቁ በምዕራባውያን ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ተቋማት ተዘግተው፣ ሕግ ወጦለት እና ሌሎች ሁነቶች ተጨምረውበት የሚከበር ሥርዓት ቢኖርም ለኢትዮጵያውያን የበዓል ስሜት አይሰጥም ብለዋል።
በምዕራባውያን ዘንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ታሪኩ ነው ያለው፤ በአብዛኛዎቹ ሀገራት በበዓላት ቀን የሃይማኖቱ ተከታዮች ቤተመቅደሶቻቸው ዝግ ናቸው፤ አማኞች ለጉብኝት፣ ለጋብቻ ቃል ለመግባት እና ለመጠመቅ ብቻ ወደ ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ ብለዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ለማክበርም እንደማይሄዱ ነው የጠቀሱት። ኢትዮጵያውያን ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሃይማኖታዊ በዓል መኾኑን በመረዳት የበዓል አከባበሩን ከቤተክርስቲያን እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
የበዓሉ አከባበር መጀመር ያለበት ከሃይማኖታዊ ሥርዓት እና ክንውን ነው ብለን ስለምናምን እርሱን እናደርጋለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ማዕድ አጋሩ።
Next articleየአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር 381 ቤቶችን ከሙሉ የቤት ዕቃና ከበዓል ማሳለፊያ ጋር በስጦታ አስረከበ።